አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 23
23
1ለዳዊትም፦ እነሆ፥ ፍልስጥኤማውያን ቅዒላን ይወጋሉ፥ አውድማውንም ይዘርፋሉ የሚል ወሬ ደረሰው። 2ዳዊትም፦ ልሂድን? እነዚህንስ ፍልስጥኤማውያን ልምታን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ፥ እግዚአብሔርም ዳዊትን፦ ሂድ፥ ፍልስጥኤማውያንን ምታ ቅዒላንም አድን አለው። 3የዳዊትም ሰዎች፦ እነሆ፥ በዚህ በይሁዳ መቀመጥ እንፈራለን፥ ይልቁንስ በፍልስጥኤማውያን ጭፍሮች ላይ ወደ ቅዒላ ብንሄድ እንዴት ነው? አሉት። 4ዳዊትም ደግሞ እግዚአብሔርን ጠየቀ፥ እግዚአብሔርም መልሶ፦ ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጣለሁና ተነሥተህ ወደ ቅዒላ ውረድ አለው። 5ዳዊትና ሰዎቹም ወደ ቅዒላ ሄዱ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ተዋጉ፥ እንስሶቻቸውንም ማረኩ፥ በታላቅም አገዳደል ገደሉአቸው። ዳዊትም በቅዒላ የሚኖሩትን አዳነ።
6እንዲህም ሆነ፥ የአቢሜሌክ ልጅ አብያታር ወደ ዳዊት ወደ ቅዒላ በኮበለለ ጊዜ ኤፉዱን ይዞ ወርዶ ነበር። 7ሳኦልም ዳዊት ወደ ቅዒላ እንደ መጣ ሰማ፥ ሳኦልም፦ መዝጊያና መወርወሪያ ወዳለባት ከተማ ገብቶ ተገኝቶአልና እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ሰጥቶታል አለ። 8ሳኦልም ወደ ቅዒላ ወርደው ይዋጉ ዘንድ፥ ዳዊትንና ሰዎቹንም ይከብቡ ዘንድ ሕዝቡን ሁሉ አዘዘ። 9ዳዊትም ሳኦል ክፉን እንዳሰበበት አወቀ፥ ካሁኑን አብያታርንም፦ ኤፉዱን ወደዚህ አምጣ አለው። 10ዳዊትም፦ የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ በእኔ ምክንያት ከተማይቱን ያጠፋ ዘንድ ሳኦል ወደ ቅዒላ ሊመጣ እንደሚፈልግ እኔ ባሪያህ ፈጽሜ ሰምቻለሁ። 11የቅዒላ ሰዎች በእጁ አሳልፈው ይሰጡኛልን? ባሪያህስ እንደ ሰማ ሳኦል በውኑ ይወርዳልን? የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ እንድትነግረኝ እለምንሃለሁ አለ። እግዚአብሔርም፦ ይወርዳል አለ። 12ዳዊትም፦ የቅዒላ ሰዎች እኔንና ሰዎቼን በሳኦል እጅ አሳልፈው ይሰጡናልን? አለ። እግዚአብሔርም፦ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ብሎ ተናገረ። 13ዳዊትና ስድስት መቶ የሚሆኑ ሰዎችም ተነሥተው ከቅዒላ ወጡ፥ መሄድም ወደሚችሉበት ሄዱ። ሳኦልም ዳዊት ከቅዒላ እንደ ሸሸ ሰማ፥ ስለዚህም ከመውጣት ቀረ።
14ዳዊትም በምድረ በዳ በአምባ ውስጥ ይኖር ነበር፥ ከዚፍ ምድረ በዳም ባለው በተራራማው አገር ተቀመጠ፥ ሳኦልም ሁልጊዜ ይፈልገው ነበር፥ እግዚአብሔር ግን በእጁ አሳልፎ አልሰጠውም። 15ዳዊትም ሳኦል ነፍሱን ሊፈልግ እንደ ወጣ አየ፥ ዳዊትም በዚፍ ምድረ በዳ በጥሻው ውስጥ ይኖር ነበር። 16የሳኦልም ልጅ ዮናታን ተነሥቶ ወደ ዳዊት ወደ ጥሻው ውስጥ ሄደ፥ እጁንም በእግዚአብሔር አጽንቶ፦ 17የአባቴ የሳኦል እጅ አታገኝህምና አትፍራ፥ አንተም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆናለህ፥ እኔም ከአንተ በታች ሁለተኛ እሆናለሁ፥ ይህን ደግሞ አባቴ ሳኦል ያውቃል አለው። 18ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረጉ፥ ዳዊትም በጥሻው ውስጥ ተቀመጠ፥ ዮናታንም ወደ ቤቱ ሄደ።
19የዚፍ ሰዎችም ወደ ሳኦል ወደ ጊብዓ መጥተው፦ እነሆ፥ ዳዊት በየሴሞን ደቡብ በኩል በኤኬላ ኮረብታ ላይ በጥሻ ውስጥ ባሉት አምባዎች በእኛ ዘንድ ተሸሽጎ የለምን? 20አሁንም፥ ንጉሥ ሆይ፥ ትወርድ ዘንድ ነፍስህ እንደ ወደደች ውረድ፥ በንጉሡም እጅ እርሱን አሳልፎ ለመስጠት እኛ አለን አሉት። 21ሳኦልም አለ፦ እናንተ ስለ እኔ አዝናችኋልና ከእግዚአብሔር ዘንድ የተባረካችሁ ሁኑ፥ 22አሁንም ደግሞ ሂዱ፥ እርሱም እጅግ ተንኮለኛ እንደ ሆነ ሰምቻለሁና አጥብቃችሁ ፈልጉት፥ እግሩም የሚሄድበትን ስፍራ እዩና እወቁ፥ በዚያ ያየውንም ሰው አግኙ። 23እርሱ የሚደበቅበትንና የሚሸሸግበትን ስፍራ እዩና እወቁ፥ በእርግጥም ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ከእናንተ ጋር እሄዳለሁ፥ በምድርም ውስጥ ቢሸሸግ በይሁዳ አእላፋት ሁሉ መካከል እፈልገዋለሁ።
24እነዚያም ተነሥተው ከሳኦል በፊት ወደዚፍ ሄዱ፥ ዳዊትና ሰዎቹ ግን በየሴሞን ደቡብ በኩል በዓረባ በማዖን ምድረ በዳ ነበሩ። 25ሳኦልና ሰዎቹም ሊፈልጉት ሄዱ፥ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ወደ ዓለቱ ወርዶ በማዖን ምድረ በዳ ተቀመጠ፥ ሳኦልም ያንን በሰማ ጊዜ ዳዊትን በማዖን ምድረ በዳ አሳደደው። 26ሳኦልም በተራራው በአንድ ወገን ሄደ፥ ዳዊትና ሰዎቹም በተራራው በሌላው ወገን ሄዱ። ሳኦልና ሰዎቹም ዳዊትንና ሰዎቹን ለመያዝ ከብበዎቸው ነበርና ዳዊት ከሳኦል ፊት ያመልጥ ዘንድ ፈጠነ። 27ወደ ሳኦልም መልእክተኛ መጥቶ፦ ፍልስጥኤማውያን አገሩን ወርረውታልና ፈጥነህ ና አለው። 28ሳኦልም ዳዊትን ማሳደድ ትቶ ተመለስ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ሊዋጋ ሄደ። ስለዚህ የዚህ ስፍራ ስም የማምለጥ ዓለት ተባለ። 29ዳዊትም ከዚያ ወጥቶ በዓይንጋዲ አምባዎች ተቀመጠ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 23: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ