አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 22
22
1ዳዊትም ከዚያ ተነሣ ወደ ዓዶላም ዋሻ ኮበለለ፥ ወንድሞቹና የአባቱም ቤት ሰው ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ እርሱ ወደዚያ ወረዱ። 2የተጨነቀም ሁሉ፥ ብድርም ያለበት ሁሉ፥ የተከፋም ሁሉ ወደ እርሱ ተከማቸ እርሱም በላያቸው አለቃ ሆነ፥ ከእርሱም ጋር አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ።
3ዳዊትም ከዚያ በሞዓብ ምድር ወዳለችው ወደ ምጽጳ ሄደ፥ የሞዓብንም ንጉሥ፦ እግዚአብሔር የሚያደርግልኝን እስካውቅ ድረስ አባቴና እናቴ ከአንተ ጋር ይቀመጡ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው። 4በሞዓብም ንጉሥ ፊት አመጣቸው፥ ዳዊትም በአምባ ውስጥ በነበረበት ወራት ሁሉ በእርሱ ዘንድ ተቀመጡ። 5ነቢዩ ጋድም ዳዊትን፦ ተነሥተህ ወደ ይሁዳ ምድር ሂድ እንጂ በአምባው ውስጥ አትቀመጥ አለው፥ ዳዊትም ተነሥቶ ወደ ሔሬት ዱር መጣ።
6ሳኦልም ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንደ ተገለጡ ሰማ። ሳኦልም በጊብዓ በአጣጥ ዛፍ በታች በኮረብታው ላይ ተቀምጦ በእጁም ጦር ይዞ ነበር፥ ባሪያዎቹም ሁሉ በአጠገቡ ቆመው ነበር። 7ሳኦልም በአጠገቡ የቆሙትን ባሪያዎቹን፦ ብንያማውያን ሆይ፥ እንግዲህ ስሙ፥ በውኑ የእሴይ ልጅ እርሻና የወይን ቦታ ለሁላችሁ ይሰጣችኋልን? ሁላችሁንስ ሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋችኋልን? 8ሁላችሁ በላዬ ዶልታችሁ ተነሣችሁብኝ፥ ልጄ ከእሴይ ልጅ ጋር ሲማማል ምንም አይገልጥልኝም፥ ከእናንተም አንድ ለእኔ የሚያዝን የለም፥ ዛሬም እንደ ሆነው ሁሉ ልጄ ባሪያዬን እንዲዶልት ሲያስነሣብኝ ማንም አላስታወቀኝም አላቸው። 9በሳኦልም ባሪያዎች አጠገብ የቆመው ኤዶማዊው ዶይቅ መልሶ፦ የእሴይ ልጅ ወደ ኖብ ወደ አኪጦብ ልጅ ወደ አቢሜሌክ ሲመጣ አይቼዋለሁ። 10እግዚአብሔርንም ጠየቀለት፥ ስንቅንም ሰጠው፥ የፍልስጥኤማዊውንም የጎልያድን ሰይፍ ሰጠው አለው።
11ንጉሡም የአኪጦብን ልጅ ካህኑን አቢሜሌክን በኖብም ያሉትን ካህናት የአባቱን ቤት ሁሉ ልኮ አስጠራቸው፥ ሁላቸውም ወደ ንጉሡ መጡ። 12ሳኦልም፦ የአኪጦብ ልጅ ሆይ፥ እንግዲህ ስማ አለ፥ እርሱም፦ እነሆኝ፥ ጌታዬ ሆይ ብሎ መለሰ። 13ሳኦልም፦ አንተና የእሴይ ልጅ ለምን ዶለታችሁብኝ? እንጀራና ሰይፍ ሰጠኸው፥ ዛሬም እንደ ተደረገው ጠላት ሆኖ ይነሣብኝ ዘንድ እግዚአብሔርን ስለ እርሱ ጠየቅህለት አለው። 14አቢሜሌክም መልሶ ንጉሡን፦ ከባሪያዎችህ ሁሉ የታመነ፥ ለንጉሥም አማች የሆነ፥ በትእዛዝህ የሚሄድ፥ በቤትህም የከበረ እንደ ዳዊት ያለ ማን ነው? 15በውኑ ስለ እርሱ እግዚአብሔርን እጠይቅ ዘንድ ዛሬ ጀመርሁን? ይህ ከእኔ ይራቅ፥ እኔ ባሪያህ ይህን ሁሉ እጅግ ወይም ጥቂት ቢሆን አላውቅምና ንጉሡ እንደዚህ ያለውን ነገር በእኔ በባሪያውና በአባቴ ቤት ሁሉ ላይ አያኑር አለ። 16ንጉሡም፦ አቢሜሌክ ሆይ፥ አንተና የአባትህ ቤት ሁሉ ፈጽማችሁ ትሞታላችሁ አለ። 17ንጉሡም በዙሪያው የቆሙትን እግረኞች፦ የእግዚአብሔር ካህናት እጅ ከዳዊት ጋር ነውና፥ ኵብለላውንም ሲያውቁ በጆሮዬ አልገለጡምና ዞራችሁ ግደሉአቸው አላቸው። የንጉሡ ባሪያዎች ግን እጃቸውን በእግዚአብሔር ካህናት ላይ ይዘረጉ ዘንድ እንቢ አሉ። 18ንጉሡም ዶይቅን፦ አንተ ዞረህ በካህናቱ ላይ ውደቅባቸው አለው። ኤዶማዊውም ዶይቅ ዞሮ በካህናቱ ላይ ወደቀ፥ በዚያም ቀን የበፍታ ኤፉድ የለበሱትን ሰማንያ አምስት ሰዎች ገደለ። 19የካህናቱም ከተማ ኖብን በሰይፍ ስለት መታ፥ ወንዶችንና ሴቶችንም፥ ብላቴኖችንና ጡት የሚጠቡትን፥ በሬዎችንና አህዮችንም በጎችንም በሰይፍ ስለት ገደለ።
20ከአኪጦብም ልጅ ከአቢሜሌክ ልጆች ስሙ አብያታር የሚባል አንዱ ልጅ አምልጦ ወደ ዳዊት ሸሸ። 21አብያታርም ሳኦል የእግዚአብሔርን ካህናት እንደ ፈጀ ለዳዊት ነገረው። 22ዳዊት አብያታርን፦ ኤዶማዊው ዶይቅ በዚያ መኖሩን ባየሁ ጊዜ፦ ለሳኦል በእርግጥ ይነግራል ብዬ በዚያው ቀን አውቄዋለሁ፥ ለአባትህ ቤት ነፍስ ሁሉ የጥፋታቸው ምክንያት እኔ ነኝ። 23ነፍሴን የሚፈልግ የአንተን ነፍስ ይፈልጋልና፥ ከእኔም ጋር ተጠብቀህ ትኖራለህና በእኔ ዘንድ ተቀመጥ፥ አትፍራ አለው።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 22: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ