የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2

2
1ሐናም ስትጸልይ እንዲህ አለች፦ ልቤ በእግዚአብሔር ጸና፥ ቀንዴ በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ አለ፥ አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ፥ በማዳንህ ደስ ብሎኛል። 2እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለምና፥ እንደ አምላካችንም ጻድቅ የለምና፥ ከአንተ በቀር ቅዱስ የለም። 3አትታበዩ፥ በኩራትም አትናገሩ፥ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ የኩራት ነገር አይውጣ። 4የኃያላንን ቀስት ሰብሮአል፥ ደካሞችም በኃይል ታጥቀዋል። 5ጠግበው የነበሩ እንጀራ አጡ፥ ተርበው የነበሩ ከራብ ዐርፈዋል፥ መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥ ብዙም የወለደችው ደክማለች። 6እግዚአብሔር ይገድላል ያድናልም፥ ወደ ሲኦል ያወርዳል፥ ያወጣል። 7እግዚአብሔር ድሀ ያደርጋል፥ ባለጠጋም ያደርጋል፥ ያዋርዳል፥ ደግሞም ከፍ ከፍ ያደርጋል። 8ከሕዝቡ መኳንንት ጋር ያስቀምጣቸው ዘንድ፥ የክብርንም ዙፋን ያወርሳቸው ዘንድ፥ ችግረኛውን ከመሬት ያስነሣል፥ ምስኪኑንም ከጉድፍ ያስነሣል፥ የምድር መሠረቶች የእግዚአብሔር ናቸውና፥ በእነርሱ ላይም ዓለምን አደረገ። 9እርሱ የቅዱሳኑን እግር ይጠብቃል ኃጥአን ግን ዝም ብለው በጨለማ ይቀመጣሉ፥ ሰው በኃይሉ አይበረታምና። 10ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ፥ በሰማይም ያንጐደጕድባቸዋል፥ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል፥ ለንጉሡም ኃይል ይሰጣል፥ የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል። 11ሕልቃናም ወደ ቤቱ ወደ አርማቴም ሄደ፥ ብላቴናውም በካሁኑ በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር።
12የዔሊም ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፥ እግዚአብሔርንም አያውቁም ነበር። 13የካህናትም ልማድ በሕዝቡ ዘንድ እንዲህ ነበረ፥ ሰው ሁሉ መሥዋዕት ሲያቀርብ ሥጋው በተቀቀለ ጊዜ የካህኑ ሎሌ ይመጣ ነበረ፥ በእጁም ሦስት ጣት ያለው ሜንጦ ነበረ፥ 14ወደ ድስቱም ወይም ወደ ምንቸቱ ወይም ወደ አፍላሉ ወይም ወደ ቶፋው ይሰድድው ነበር፥ ሜንጦውም ያወጣውን ሁሉ ካህኑ ለእርሱ ይወስደው ነበር። ወደዚያም በመጡት በእስራኤላውያን ላይ በሴሎ እንዲህ ያደርጉ ነበር። 15ደግሞም ስቡን ሳያቃጥሉ የካህኑ ሎሌ መጥቶ የሚሠዋውን ሰው፦ ጥሬውን እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ አይወስድምና እጠብስለት ዘንድ ለካህኑ ሥጋ ስጠኝ ይለው ነበር። 16ሰውዮውም፦ አስቀድሞ ስቡን ያቃጥሉት ኋላም ሰውነትህ ደስ የሚያሰኛትን ትወስዳለህ ቢለው፥ እርሱ፦ አይሆንም፥ ነገር ግን አሁን ስጠኝ፥ እንቢም ብትል በግድ እወስደዋለሁ ይለው ነበር። 17ሰዎቹም የእግዚአብሔርን ቁርባን ይንቁ ነበርና የጎበዛዝቱ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበረች።
18ሳሙኤል ግን ገና ብላቴና ሳለ የበፍታ ኤፋድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር። 19እናቱም ታናሽ መደረቢያ ሠራችለት፥ በየዓመቱም መሥዋዕት ለመሠዋት ከባልዋ ጋር ስትወጣ ታመጣለት ነበር። 20ዔሊም ሕልቃናንና ሚስቱን፦ ለእግዚአብሔር ስለ ተሳለችው ስጦታ ፋንታ ከዚህች ሴት እግዚአብሔር ዘር ይስጥህ ብሎ ባረካቸው፥ እነርሱም ወደ ቤታቸው ሄዱ። 21እግዚአብሔርም ሐናን አሰበ፥ ፀነሰችም፥ ሦስት ወንዶችና ሁለትም ሴቶች ልጆች ወለደች። ብላቴናውም ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት አደገ።
22ዔሊም እጅግ አረጀ፥ ልጆቹም በእስራኤል ሁሉ ላይ ያደረጉትን ሁሉ፥ በመገናኛውም ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር እንደ ተኙ ሰማ። 23እርሱም አላቸው፦ ስለ ክፉ ሥራችሁ ከዚህ ሕዝብ ሁሉ ሰምቻለሁና ስለምን እንዲህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ? 24ልጆቼ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢአተኛ በማድረጋችሁ ስለ እናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምና ይህ አይሆንም። 25ሰውስ ሰውን ቢበድል እግዚአብሔር ይፈርድበታል ሰው ግን እግዚአብሔርን ቢበድል ስለ እርሱ የሚለምን ማን ነው? እነርሱ ግን እግዚአብሔር ሊገድላቸው ወድዶአልና የአባታቸውን ቃል አልሰሙም። 26ብላቴናውም ሳሙኤል እያደገ ሄደ፥ በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት ሞገስ እያገኘ ሄደ።
27የእግዚአብሔርም ሰው ወደ ዔሊ መጥቶ አለው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ በግብጽ በፈርዖን ቤት ባሪያ ሳለ ለአባትህ ቤት ተገለጥሁ፥ 28ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ ካህን ይሆነኝ ዘንድ፥ በመሠዊያዬ ላይ ይሠዋ ዘንድ፥ ዕጣንንም ያጥን ዘንድ ኤፋድንም በፊቴ ይለብስ ዘንድ ለእኔ መረጥሁት፥ የእስራኤልንም ልጆች የእሳት ቍርባን ሁሉ ስለ ምግብ ለአባትህ ቤት ሰጠሁ። 29በማደሪያዬ ያቀርቡት ዘንድ ያዘዝሁትን መሥዋዕቴንና ቍርባኔን ስለ ምን ረገጣችሁ? እንድትወፍሩም የሕዝቤን የእስራኤልን ቍርባን ሁሉ መጀመሪያ በመብላታችሁ ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ለምን አከበርህ? 30ስለዚህም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእውነት ቤትህ የአባትህም ቤት ለዘላለም በፊቴ እንዲኖር ተናግሬአለሁ፥ አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያከበሩኝን አከብራለሁና፥ የናቁኝም ይናቃሉና ይህ አይሆንልኝም። 31እነሆ፥ ለቤትህ ሽማግሌ እንዳይገኝ፥ ክንድህን የአባትህንም ቤት ክንድ የምሰብርበት ዘመን ይመጣል። 32በእስራኤል በረከት ሁሉ፥ በማደሪያዬ ጠላትህን ታያለህ በቤትህም ለዘላለም ሽማግሌ አይገኝም። 33ከመሠዊያዬ ያልተቆረጠ ልጅህ ቢገኝ ዓይንህን ያፈዝዘዋል፥ ነፍስህንም ያሳዝናል ከቤትህም የሚወለዱ ሰዎች ሁሉ በጎልማስነት ይሞታሉ። 34ይህ በሁለቱ ልጆችህ በአፍኒንና በፊንሐስ ላይ የሚመጣ ለአንተ ምልክት ነው፥ ሁለቱ በአንድ ቀን ይሞታሉ። 35የታመነም ካህን ለእኔ አስነሣለሁ፥ በልቤም በነፍሴም እንዳለ እንዲሁ ያደርጋል፥ እኔም የታመነ ቤት እሠራለታለሁ፥ ዘመኑን ሁሉ እኔ በቀባሁት ሰው ፊት ይሄዳል። 36ከቤትህም የቀረው ሁሉ ይመጣል፥ በፊቱም ሰግዶ፦ ቁራሽ እንጀራ እበላ ዘንድ ከካህናት ወደ አንዲቱ ዕጣ፥ እባክህ፥ ስደደኝ ብሎ አንድ ብር አንድ እንጀራም ይለምናል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ