የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17:32-49

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17:32-49 አማ54

ዳዊትም ሳኦልን፦ ስለ እርሱ የማንም ልብ አይውደቅ፥ እኔ ባሪያህ ሄጄ ያንን ፍልስጥኤማዊ እወጋዋለሁ አለው። ሳኦልም ዳዊትን፦ አንተ ገና ብላቴና ነህና፥ እርሱም ከብላቴንነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነውና ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም አለው። ዳዊትም ሳኦልን አለው፦ እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳና ድብ ይመጣ ነበር፥ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር። በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፥ ከአፉም አስጥለው ነበር፥ በተነሣብኝም ጊዜ ጉሮሮውን ይዤ እመታውና እገድለው ነበር። እኔ ባሪያህ አንበሳና ድብ መታሁ፥ ይህም ያልተገረዘው ፍልስጥኤማዊ የሕያውን አምላክ ጭፍሮች ተገዳድሮአልና ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ዳዊትም፦ ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል አለ። ሳኦልም ዳዊትን፦ ሂድ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል አለው። ሳኦልም ዳዊትን የገዛ ራሱን ልብስ አለበሰው፥ በራሱም ላይ የናስ ቁር ደፋለት፥ ጥሩርም አለበሰው። ዳዊትም ሰይፉን በልብሱ ላይ ታጠቀ፥ ገናም አልፈተነውምና መሄድ ሞከረ። ዳዊትም ሳኦልን፦ አልፈተንሁትምና እንዲህ ብዬ መሄድ አልችልም አለው። ዳዊትም አወለቀ። በትሩንም በእጁ ወሰደ፥ ከወንዝም አምስት ድብልብል ድንጋዮችን መረጠ፥ በእረኛ ኮረጆውም በኪሱ ከተታቸው፥ ወንጭፍም በእጁ ነበረ፥ ወደ ፍልስጥኤማዊውም ቀረበ። ፍልስጥኤማዊውም መጥቶ ወደ ዳዊት ቀረበ፥ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። ጎልያድም ዳዊትን ትኩር ብሎ አየው፥ ቀይ ብላቴና መልኩም ያማረ ነበረና ናቀው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፦ በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን? አለው። ፍልስጥኤማዊውም በአምላኮቹ ስም ዳዊትን ረገመው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፦ ወደ እኔ ና፥ ሥጋህንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን አለው፦ አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ፥ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፥ እመታህማለሁ፥ ራስህንም ከአንተ አነሣዋለሁ፥ የፍልስጥኤማውያንንም ሠራዊት ሬሶች ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ዛሬ እሰጣለሁ። ይኸውም ምድር ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ታውቅ ዘንድ፥ ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደል ያውቅ ዘንድ ነው። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፥ እናንተንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል። ፍልስጥኤማዊውም ተነሥቶ ዳዊትን ሊገናኘው በቀረበ ጊዜ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ሊገናኘው ወደ ሰልፉ ሮጠ። ዳዊትም እጁን ወደ ኮረጆው አግብቶ አንድ ድንጋይ ወሰደ፥ ወነጨፈውም፥ ፍልስጥኤማዊውንም ግምባሩን መታ፥ ድንጋዩም በግምባሩ ተቀረቀረ፥ እርሱም በምድር ላይ በፊቱ ተደፋ።