የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15

15
1ሳሙኤልም ሳኦልን አለው፦ በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንድትሆን እቀባህ ዘንድ እግዚአብሔር ላከኝ፥ አሁንም የእግዚአብሔርን ድምፅ ስማ። 2የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ አማሌቅ በመንገድ እየተቃወመ ያደረገበትን እበቀላለሁ። 3አሁንም ሄደህ አማሌቅን ምታ፥ ያላቸውንም ሁሉ ፈጽመህ አጥፋ፥ አትማራቸውም፥ ወንዱንና ሴቱን ብላቴናውንና ሕፃኑን በሬውንና በጉን ግመሉንና አህያውን ግደል።
4ሳኦልም ሕዝቡን ጠርቶ በጌልገላ ቆጠራቸው፥ ሁለት መቶ ሺህ እግረኞች፥ ከይሁዳም አሥር ሺህ ሰዎች ነበሩ። 5ሳኦልም ወደ አማሌቅ ከተማ ወጣ፥ በሸለቆውም ውስጥ ተደበቀ። 6ሳኦል ቄናውያንን፦ ተነሥታችሁ ሂዱ፥ ከግብጽ በወጡ ጊዜ ለእስራኤል ልጆች ቸርነት አድርጋችኋልና ከአማሌቅ ጋር እንዳላጠፋችሁ ከመካከላቸው ውረዱ አላቸው፥ ቄናውያንም ከአማሌቃውያን መካከል ሄዱ። 7ሳኦልም አማሌቃውያንን ከኤውላጥ ጀምሮ በግብጽ ፊት እስካለችው እስከ ሱር ድረስ መታቸው። 8የአማሌቅንም ንጉሥ አጋግን በሕይወቱ ማረከው፥ ሕዝቡንም ሁሉ በሰይፍ ስለት ፈጽሞ አጠፋቸው። 9ነገር ግን ሳኦልና ሕዝቡ ለአጋግ፥ ለተመረጡትም በጎችና በሬዎች ለሰቡትም ጥጆችና ጠቦቶች፥ ለመልካሞቹም ሁሉ ራሩላቸው፥ ፈጽሞ ሊያጠፉአቸውም አልወደዱም፥ ነገር ግን ምናምንቴንና የተናቀውን ሁሉ ፈጽመው አጠፉት።
10የእግዚአብሔርም ቃል፦ ሳኦል እኔን ከመከተል ተመልሶአልና፥ 11ትእዛዜንም አልፈጸመምና ስላነገሥሁት ተጸጸትሁ ብሎ ወደ ሳሙኤል መጣ። ሳሙኤልም ተቆጣ፥ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጮኽ። 12ሳሙኤልም በነጋው ሳኦልን ለመገናኘት ማለደ፦ ሳኦልም ወደ ቀርሜሎስ መጣ፥ እነሆም፥ የመታሰቢያ ዓምድ ባቆመ ጊዜ ዞሮ አለፈ፥ ወደ ጌልገላም ወረደ የሚል ወሬ ለሳሙኤል ደረሰለት። 13ሳሙኤልም ወደ ሳኦል መጣ፥ ሳኦልም፦ አንተ ለእግዚአብሔር የተባረክህ ሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ አለው። 14ሳሙኤልም፦ ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ጩኸትና የበሬዎች ግሣት ምንድር ነው? አለ። 15ሳኦልም፦ ሕዝቡ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ይሠዉአቸው ዘንድ መልካሞቹን በጎችና በሬዎች አድነዋቸዋልና ከአማሌቃውያን አምጥተዋቸዋል፥ የቀሩትንም ፈጽመን አጠፋን አለው። 16ሳሙኤልም ሳኦልን፦ ቆይ፥ እግዚአብሔር ዛሬ ሌሊት የነገረኝን ልንገርህ አለው፥ እርሱም፦ ተናገር አለው።
17ሳሙኤልም አለ፦ በዓይንህ ምንም ታናሽ ብትሆን ለእስራኤል ነገዶች አለቃ አልሆንህምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባህ። 18እግዚአብሔርም፦ ሄደህ ኃጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፥ እስኪጠፉም ድረስ ውጋቸው ብሎ በመንገድ ላከህ። 19ለምርኮ ሳስተህ ለምን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህም? ለምንስ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረግህ? 20ሳኦልም ሳሙኤልን፦ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቻለሁ፥ እግዚአብሔርም በላከኝ መንገድ ሄጃለሁ፥ የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጥቻለሁ፥ አማሌቃውያንንም ፈጽሜ አጥፍቻለሁ። 21ሕዝቡ ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በጌልገላ ይሠዉ ዘንድ ከእርሙ የተመረጡትን በጎችንና በሬዎችን ከምርኮው ወሰዱ አለው። 22ሳሙኤልም፦ በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል። 23ዓመፀኝነት እንደ ምዋርተኛ ኃጢአት፥ እልከኝነትም ጣዖትንና ተራፊምን እንደ ማምለክ ነው፥ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እግዚአብሔር ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ አለ።
24ሳኦልም ሳሙኤልን፦ ሕዝቡን ስለ ፈራሁ፥ ቃላቸውንም ስለ ሰማሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና የአንተን ቃል በመተላለፍ በድያለሁ። 25አሁንም፥ እባክህ፥ ኃጢአቴን ይቅር በለኝ፥ ለእግዚአብሔርም እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመለስ አለው። 26ሳሙኤልም ሳኦልን፦ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና፥ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃልና ከአንተ ጋር አልመለስም አለው። 27ሳሙኤልም ሊሄድ ዘወር ባለ ጊዜ ሳኦል የልብሱን ጫፍ ያዘ፥ ተቀደደም። 28ሳሙኤልም፦ እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀደዳት፥ ከአንተም ለሚሻል ለጎረቤትህ አሳልፎ ሰጣት፥ 29የእስራኤል ኃይል እንደ ሰው የሚጸጸት አይደለምና አይዋሽም አይጸጸትምም አለው። 30እርሱም፦ በድያለሁ፥ አሁን ግን በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊትና በእስራኤል ፊት፥ እባክህ፥ አክብረኝ፥ ለአምላክህም ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተምለስ አለው። 31ሳሙኤልም ከሳኦል በኋላ ተመለሰ፥ ሳኦልም ለእግዚአብሔር ሰገደ።
32ሳሙኤልም፦ የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጡልኝ አለ። አጋግም እየተንቀጠቀጠ ወደ እርሱ መጣ። አጋግም፦ በውኑ ሞት እንደዚህ መራራ ነውን? አለ። 33ሳሙኤልም፦ ሰይፍህ ሴቶችን ልጆች አልባ እንዳደረገቻቸው እንዲሁ እናትህ በሴቶች መካከል ልጅ አልባ ትሆናለች አለ፥ ሳሙኤልም አጋግን በእግዚአብሔር ፊት በጌልገላ ቆራረጠው።
34ሳሙኤልም ወደ አርማቴም ሄደ፥ 35ሳኦልም ወደ ቤቱ ወደ ጊብዓ ወጣ። ሳሙኤልም እስከ ሞተበት ቀን ድረስ ሳኦልን ለማየት ዳግመኛ አልሄደም፥ ሳሙኤልም ለሳኦል አለቀሰ፥ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ሳኦልን ስላነገሠ ተጸጸተ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ