አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 14
14
1አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፥ የሳኦል ልጅ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን፦ ና፥ በዚያ በኩል ወዳለው ወደ ፍልስጥኤማውያን ጭፍራ እንለፍ አለው፥ ለአባቱም አልነገረውም። 2ሳኦልም በመጌዶን ባለው በሮማኑ ዛፍ በታች በጊብዓ ዳርቻ ተቀምጦ ነበር፥ ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ስድስት መቶ የሚያህል ሰው ነበረ። 3የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ የፊንሐስ ልጅ የዔሊ ልጅ በሴሎ ለእግዚአብሔር ካህን የሆነ ኤፉድም የለበሰ አኪያ አብሮ ነበር፥ ሕዝቡ ዮናታን እንደ ሄደ አላወቁም። 4ዮናታንም ወደ ፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ሊሻገርበት በወደደው መተላለፊያ መካከል በወዲህ አንድ ሾጣጣ በወዲህ አንድ ሾጣጣ ድንጋዮች ነበሩ፥ የአንዱም ስም ቦጼጽ የሁለተኛውም ስም ሴኔ ነበረ። 5አንዱም ሾጣጣ በማክማስ አንጻር በሰሜን በኩል፥ ሁለተኛውም በጊብዓ አንጻር በደቡብ በኩል የቆሙ ነበሩ።
6ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን፦ ና፥ ወደ እነዚህ ቆላፋን ጭፍራ እንለፍ፥ በብዙ ወይም በጥቂቱ ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና ምናልባት እግዚአብሔር ይሠራልን ይሆናል አለው። 7ጋሻ ጃግሬውም፦ ልብህ ያሰኘህን ሁሉ አድርግ፥ እነሆ፥ ከአንተ ጋር ነኝ፥ እንደ አንተ ልብ ሁሉ የእኔም ልብ እንዲሁ ነው አለው። 8ዮናታንም አለ፦ እነሆ፥ ወደ ሰዎቹ እናልፋለን እንገለጥላቸውማለን፥ 9እነርሱም፦ ወደ እናንተ እስክንመጣ ድረስ ቆዩ ቢሉን በስፍራችን እንቆማለን፥ ወደ እነርሱም አንወጣም። 10ነገር ግን፦ ወደ እኛ ውጡ ቢሉን እግዚአብሔር በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና እንወጣለን፥ ምልክታችንም ይህ ይሆናል። 11ሁለታቸውም ለፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ተገለጡ፥ ፍልስጥኤማውያንም፦ እነሆ፥ ዕብራውያን ከተሸሸጉበት ጉድጓድ ይወጣሉ አሉ። 12የጭፍራው ሰዎችም ዮናታንንና ጋሻ ጃግሬውን፦ ወደ እኛ ውጡ፥ አንድ ነገርም እናሳያችኋለን አሉ። ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን፦ እግዚአብሔር በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና ተከተለኝ አለው። 13ዮናታንም በእጁና በእግሩ ወጣ፥ ጋሻ ጃግሬውም ተከተለው፥ ፍልስጥኤማውያንም በዮናታን እጅ ወደቁ፥ ጋሻ ጃግሬውም ተከትሎ ገደላቸው። 14የዮናታንና የጋሻ ጃግሬውም የመጀመሪያ ግዳያቸው በአንድ ትልም እርሻ መካከል ሀያ ያህል ሰው ነበረ። 15በሰፈሩም በእርሻውና በሕዝቡም ሁሉ መካከል ሽብር ነበረ፥ በሰፈሩ የተቀመጡና ለምርኮ የወጡት ተሸበሩ፥ ምድሪቱም ተናወጠች፥ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ታላቅ ሽብር ሆነ። 16በብንያም ጊብዓ ያሉ የሳኦል ዘበኞችም ተመለከቱ፥ እነሆም፥ ሠራዊቱ ወዲህና ወዲያ እየተራወጡ ተበታተኑ። 17ሳኦልም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ፦ እስኪ ተቋጠሩ፥ ከእኛ ዘንድ የሄደ ማን እንደሆነ ተመልከቱ አላቸው። በተቋጠሩም ጊዜ እነሆ፥ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልነበሩም። 18በዚያም ቀን አኪያ በእስራኤል ልጆች ፊት ኤፉድ ለብሶ ነበርና ሳኦል፦ ኤፉድን አምጣ አለው። 19ሳኦል ከካህኑ ጋር ሲነጋገር በፍልስጥኤማውያን ሰፈር ግርግርታ እየበዛና እየጠነከረ ሄደ፥ ሳኦልም ካህኑን፦ እጅህን መልስ አለው። 20ሳኦልና ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተሰብስበው ወደ ውጊያው መጡ፥ እነሆም፥ የእያንዳንዱ ሰው ሰይፍ በባልንጀራው ላይ ነበረ፥ እጅግም ታላቅ ድንጋጤ ሆነ። 21ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጋር የነበሩት ከእነርሱም ጋር ከሰፈሩ ዙሪያ የወጡት ዕብራውያን ደግሞ ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ወደ ነበሩት እስራኤላውያን ለመሆን ዞሩ። 22ከእስራኤልም ሰዎች በተራራማው በኤፍሬም አገር የተሸሸጉት ሁሉ ፍልስጥኤማውያን እንደ ኮበለሉ በሰሙ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ሊዋጉአቸው ተከትለው ገሠገሡ። 23እግዚአብሔርም በዚያ ቀን እስራኤልን አዳን፥ ውጊያውም በቤትአዌን በኩል አለፈ። ከሳኦልም ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ አሥር ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ፥ ውጊያውም በተራራማው በኤፍሬም አገር ሁሉ ተበታትኖ ነበር። 24የእስራኤልም ሰዎች በዚያ ቀን ተጨነቁ፥ ሳኦል፦ ጠላቶቼን እስክበቀል እስከ ማታ ድረስ መብል የሚበላ ሰው ርጉም ይሁን ብሎ ሕዝቡን አምሎአቸው ነበርና። ሕዝቡም ሁሉ መብል አልቀመሱም። 25ሕዝቡም ሁሉ ወደ ዱር ገባ፥ ማርም በምድር ላይ ነበረ። 26ሕዝቡም ወደ ዱር በገባ ጊዜ እነሆ፥ የሚፈስስ ማር ነበር፥ ሕዝቡ መሐላውን ፈርቶ ነበርና ማንም እጁን ወደ አፉ አላደረገም። 27ዮናታን ግን አባቱ ሕዝቡን ባማለ ጊዜ አልሰማም ነበር፥ እርሱም በእጁ ያለችውን በትር ጫፍዋን ወደ ወለላው ነከረ፥ እጁንም ወደ አፉ አደረገ፥ ዓይኑም በራ። 28ከሕዝቡም አንድ ሰው መልሶ፦ አባትህ፦ ዛሬ መብል የሚበላ ሰው ርጉም ይሁን ብሎ ሕዝቡን መሐላ አምሎአቸዋል አለው፥ ሕዝቡም ደከሙ። 29ዮናታንም፦ አባቴ ምድሪቱን አስቸገረ፥ ከዚህ ማር ጥቂት ብቀምስ ዓይኔ እንደ በራ እዩ። 30ይልቅስ ሕዝቡ ካገኙት ከጠላቶቻቸው ምርኮ በልተው ቢሆኑ የፍልስጥኤማውያን መመታት ይበልጥ አልነበረምን? አለ።
31በዚያም ቀን ፍልስጥኤማውያንን ከማክማስ እስከ ኤሎን ድረስ መቱአቸው፥ ሕዝቡም እጅግ ደከሙ። 32ሕዝቡም ለምርኮ ሳሱ፥ በጎችን በሬዎችንም ጥጆችንም ወስደው በምድር ላይ አረዱ፥ ሕዝቡም ከደሙ ጋር በሉ። 33ለሳኦልም፦ እነሆ፥ ሕዝቡ ከደሙ ጋር በመብላታቸው እግዚአብሔርን በደሉ ብለው ነገሩት። ሳኦልም፦ እጅግ ተላለፋችሁ፥ አሁንም ትልቅ ድንጋይ አንከባልላችሁ አቅርቡልኝ አላቸው። 34ሳኦልም፦ በሕዝቡ መካከል እየዞራችሁ፦ እያንዳንዱ ሰው በሬውንና በጉን ወደ እኔ ያቅርብ፥ በዚህም እረዱና ብሉ፥ ከደሙም ጋር በመብላታችሁ እግዚአብሔርን አትበድሉ በሉአቸው አለ። እያንዳንዱም ሰው ሁሉ በእጁ ያለውን በሬውን በዚያች ሌሊት አቀረበ፥ በዚያም አረደው። 35ሳኦልም ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ፥ ይኸውም ለእግዚአብሔር የሠራው መጀመሪያ መሠዊያ ነው።
36ሳኦልም፥ ፍልስጥኤማውያንን በሌሊት ተከትለን እስኪነጋ ድረስ እንበዝብዛቸው አንድ ሰው እንኳ አናስቀርላቸው አለ። እነርሱም፦ ደስ የሚያሰኝህን ሁሉ አድርግ አሉት። ካህኑም፦ ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ አለ። 37ሳኦልም፦ ፍልስጥኤማውያንን ልከተልን? በእስራኤልስ እጅ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀው። በዚያ ቀን ግን አልመለሰለትም። 38-39ሳኦልም፦ እናንተ የሕዝቡ አለቆች ሁሉ፥ ወደዚህ ቅረቡ፥ ዛሬ ይህ ኃጢአት በምን እንደ ሆነ እወቁ፥ ተመልከቱም፥ እስራኤልን የሚያድን ሕያው እግዚአብሔርን! ኃጢአቱ በልጄ በዮናታን ቢሆን ፈጽሞ ይሞታል አለ። ከሕዝቡም ሁሉ አንድ የመለሰለት ሰው አልነበረም። 40እስራኤልንም ሁሉ፦ እናንተ በአንድ ወገን ሁኑ፥ እኔና ልጄ ዮናታንም በሌላ ወገን እንሆናለን አለ። ሕዝቡም ሳኦልን ደስ የሚያሰኝህን አድርግ አሉት። 41ሳኦልም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን፦ እውነትን ግለጥ አለው። ሳኦልና ዮናታንም ተያዙ፥ ሕዝቡም ነጻ ሆነ። 42ሳኦልም፦ በእኔና በልጄ በዮናታን መካከል ዕጣ ጣሉ አለ። ዮናታንም ተያዘ።
43ሳኦልም ዮናታንን፦ ያደረግኸውን ንገረኝ አለው፥ ዮናታንም፦ በእጄ ባለው በበትሬ ጫፍ ጥቂት ማር በእርግጥ ቀምሻለሁ፥ እነሆኝ፥ እሞታለሁ ብሎ ነገረው። 44ሳኦልም፦ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብኝ እንዲህም ይጨምርብኝ፥ ዮናታን ሆይ፥ ፈጽመህ ትሞታለህ አለ። 45ሕዝቡም ሳኦልን፦ በውኑ በእስራኤል ዘንድ ታላቅ መድኃኒት ያደረገ ዮናታን ይሞታልን? ይህ አይሁን፥ ዛሬ ከእግዚአብሔር ጋር አድርጎአልና ሕያው እግዚአብሔርን! ከራሱ ጠጉር አንዲት በምድር ላይ አትወድቅም አሉት። ሕዝቡም እንዳይሞት ዮናታንን አዳነው። 46ሳኦልም ፍልስጥኤማውያንን ከመከተል ተመለሰ፥ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ስፍራቸው ሄዱ። 47ሳኦልም መንግሥቱን በእስራኤል ላይ አጸና፥ በዙሪያውም ካሉት ከጠላቶቹ ሁሉ ጋር፥ ከሞዓብም፥ ከአሞንም ልጆች፥ ከኤዶምያስም፥ ከሱባም ነገሥታት፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ይዋጋ ነበር፥ በየሄደበትም ሁሉ ድል ይነሣ ነበር። 48እርሱም ጀግና ነበረ፥ አማሌቃውያንንም መታ፥ እስራኤልንም ከዘራፊዎቹ እጅ አዳነ።
49የሳኦልም ወንዶች ልጆች ዮናታን፥ የሱዊ፥ ሚልኪሳ ነበሩ፥ የሁለቱም ሴቶች ልጆቹ ስም ይህ ነበረ፥ የታላቂቱ ስም ሜሮብ፥ የታናሺቱም ስም ሜልኮል ነበረ። 50የሳኦልም ሚስት ስም የአኪማአስ ልጅ አኪናሆም ነበረ፥ የሠራዊቱም አለቃ ስም የሳኦል አጎት የኔር ልጅ አበኔር ነበረ። 51የሳኦልም አባት ቂስ ነበረ፥ የአበኔርም አባት ኔር የአቢኤል ልጅ ነበረ።
52በሳኦልም ዕድሜ ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጽኑ ውጊያ ነበረ፥ ሳኦልም ጽኑ ወይም ኃያል ሰው ባየ ጊዜ ወደ እርሱ ይሰበስብ ነበር።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 14: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ