የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 10

10
1ሳሙኤልም የዘይቱን ብርሌ ወስዶ በራሱ ላይ አፈሰሰው፥ ሳመውም፥ እንዲህም አለው፦ በርስቱ ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶሃል፥ የእግዚአብሔርንም ሕዝብ ትገዛለህ፥ በዙሪያውም ካሉ ጠላቶቻቸው እጅ ታድናቸዋለህ። 2ዛሬ ከእኔ በተለየህ ጊዜ በብንያም ዳርቻ በጼልጻህ አገር ባለው በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ፥ እነርሱም፦ ልትሻቸው ሄደህ የነበርህላቸው አህዮች ተገኝተዋል፥ እነሆም፥ አባትህ ስለ አህዮች ማሰብ ትቶ፥ የልጄን ነገር እንዴት አደርጋለሁ? እያለ ስለ እናንተ ይጨነቃል ይሉሃል። 3ከዚያም ደግሞ ወደ ፊት ትሄዳለህ፥ ወደ ታቦር ወደ ትልቁ ዛፍ ትደርሳለህ፥ በዚያም ሦስት ሰዎች፥ አንዱ ሦስት የፍየል ጠቦቶች፥ ሁለተኛው ሦስት ዳቦ፥ ሦስተኛውም የወይን ጠጅ አቁማዳ ይዘው ወደ እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ሲወጡ ያገኙሃል፥ 4ሰላምታም ይሰጡሃል፥ ሁለትም ዳቦ ይሰጡሃል፥ ከእጃቸውም ትቀበላለህ። 5ከዚያም በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ኮረብታ ትመጣለህ፥ ወደዚያም ወደ ከተማይቱ በደረስህ ጊዜ፥ በገናና ከበሮ እምቢልታና መሰንቆ ይዘው ትንቢት እየተናገሩ ከኮረብታው መስገጃ የሚወርዱ የነቢያት ጉባኤ ያገኙሃል። 6የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ይወርድብሃል፥ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ትናገራለህ፥ እንደ ሌላ ሰውም ሆነህ ትለወጣለህ። 7እነዚህም ምልክቶች በደረሱህ ጊዜ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና እጅህ የምታገኘውን ሁሉ አድርግ። 8በፊቴም ወደ ጌልገላ ትወርዳለህ፥ እኔም፥ እነሆ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀርብ ዘንድ፥ የደኅንነትም መሥዋዕት እሠዋ ዘንድ ወደ አንተ እወርዳለሁ፥ እኔ ወደ አንተ እስክመጣና የምታደረገውን እስክነግረህ ድረስ ሰባት ቀን ትቆያለህ።
9ከሳሙኤልም ዘንድ ለመሄድ ፊቱን በመለሰ ጊዜ እግዚአብሔር ሌላ ልብ ለወጠለት፥ በዚያም ቀን እነዚህ ምልክቶች ሁሉ ደረሱለት። 10ወደዚያም ኮረብታ በደረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ የነቢያት ጉባኤ አገኙት፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ወረደበት፥ በመካከላቸውም ትንቢት ተናገረ። 11ቀድሞም የሚያውቁት ሁሉ ከነቢያት ጋር ትንቢት ሲናገር ባዩት ጊዜ ሕዝቡ እርስ በርሳቸው፦ የቂስን ልጅ ያገኘው ምንድር ነው? በውኑ ሳኦል ከነቢያት ወገን ነውን? ተባባሉ። 12ከዚያም ስፍራ ያለ አንድ ሰው፦ አባታቸውስ ማን ነው? ብሎ መለሰ። ስለዚህም፦ ሳኦል ደግሞ ከነቢያት ወገን ነውን? የሚል ምሳሌ ሆነ። 13ትንቢት መናገሩንም በፈጸመ ጊዜ ወደ ኮረብታው መስገጃ መጣ። 14አጎቱም ሳኦልንና ብላቴናውን፦ ወዴት ሄዳችሁ ኖርአል? አላቸው። እርሱም፦ አህዮችን ልንሻ ሄደን ነበር፥ ባጣናቸውም ጊዜ ወደ ሳሙኤል መጣን አለ። 15የሳኦልም አጎት፦ ሳሙኤል የነገረህን፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለው። 16ሳኦልም አጎቱን፦ አህዮች እንደ ተገኙ ገለጠልን አለው፥ ነገር ግን ሳሙኤልን የነገረውን የመንግሥትን ነገር አላወራለትም።
17ሳሙኤልም ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ጠራ። 18የእስራኤልንም ልጆች የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስራኤልን ከግብጽ አወጣሁ፥ ከግብጻውያንም እጅ ከሚያስጨንቁአችሁም ነገሥታት ሁሉ እጅ አዳንኋችሁ። 19ዛሬ ግን ከመከራችሁና ከጭንቃችሁ ሁሉ ያዳናችሁን አምላክቻሁን ንቃችሁ፦ እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ አንግሥልን አላችሁት። አሁንም በየነገዳችሁና በየወገናችሁ ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ አላቸው። 20ሳሙኤልም የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ አቀረበ፥ ዕጣውም በብንያም ነገድ ላይ ወደቀ። 21የብንያምንም ነገድ በየወገናቸው አቀረበ፥ ዕጣውም በማጥሪ ወገን ላይ ወደቀ። የማጥሪንም ወገን በየሰዉ አቀረበ፥ ዕጣውም በቂስ ልጅ በሳኦል ላይ ወደቀ፥ ፈለጉትም፥ አላገኙትምም። 22ከእግዚአብሔርም፦ ገና ወደዚህ የሚመጣ ሰው አለን? ብለው ደግሞ ጠየቁት እግዚአብሔርም፦ እነሆ፥ በዕቃ መካከል ተሸሽጎአል ብሎ መለሰ። 23እነርሱም ሮጠው ከዚያ አመጡት፥ እርሱም በሕዝቡ መካከል ቆመ፥ ከሕዝቡም ሁሉ ይልቅ ከትከሻው ወደ ላይ ከፍ ያለ ቁመተ ረጅም ነበረ። 24ሳሙኤልም ለሕዝቡ ሁሉ፦ ከሕዝቡ ሁሉ እርሱን የሚመስል እንደሌለ እግዚአብሔር የመረጠውን ታያላችሁን? አላቸው፥ ሕዝቡም ሁሉ፦ ንጉሥ ሕያው ይሁን እያሉ እልልታ አደረጉ።
25ሳሙኤልም የመንግሥቱን ወግ ነገረ፥ በመጽሐፍም ጻፈው በእግዚአብሔርም ፊት አኖረው። ሳሙኤልም ሕዝቡን ሁሉ ወደ እየቤታቸው አሰናበታቸው። 26ሳኦልም ወደ ቤቱ ወደ ጊብዓ ሄደ፥ እግዚአብሔር ልባቸውን የነካ ኃያላንም ከእርሱ ጋር ሄዱ። 27ምናምንቴዎች ሰዎች ግን፦ ይህ ሰው እንዴት ያድነናል? ብለው ናቁት፥ እጅ መንሻም አላመጡለትም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ