አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 9
9
እግዚአብሔር ለሰሎሞን እንደገና መገለጡ
(2ዜ.መ. 7፥11-22)
1ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት፥ የንጉሡን ቤትና ሰሎሞን የወደደውን የልቡን አሳብ ሁሉ ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ፥ 2እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን እንደ ተገለጠለት ዳግመኛ ተገለጠለት። 3እግዚአብሔርም አለው “በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዐይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ። 4ዳዊትም አባትህ በየዋህ ልብና በቅንነት እንደ ሄደ አንተ ደግሞ በፊቴ ብትሄድ፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ሥርዐቴንም ፍርዴንም ብትጠብቅ፥ 5እኔ ‘ከእስራኤል ዙፋን ከዘርህ ሰው አታጣም፤’ ብዬ ለአባትህ ለዳዊት እንደ ተናገርሁ፥ የመንግሥትህን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ። 6እናንተና ልጆቻችሁ ግን እኔን ከመከትል ብትመለሱ፥ የሰጠኋችሁንም ትእዛዜንና ሥርዐቴን ባትጠብቁ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ ብትሰግዱላቸውም፥ 7እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለሁ፤ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ፤ እስራኤልም በአሕዛብ ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት ይሆናሉ። 8ከፍ ከፍ ብሎ የነበረው ይህ ቤት ባድማ ይሆናል፤ በዚያም የሚያልፍ ሁሉ እያፍዋጨ ‘እግዚአብሔር በዚህ አገርና በዚህ ቤት ስለምን እንዲህ አደረገ?’ ብሎ ይደነቃል። 9መልሰውም ‘ከግብጽ ምድር አባቶቻቸውን ያወጣውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችን አማልክት ስለ ተከተሉ፥ ስለ ሰገዱላቸውም፥ ስለ አመለኩአቸውም፥ ስለዚህ እግዚአብሔር ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣባቸው፤’ ይላሉ።”
ሰሎሞን ያከናወናቸው ሌሎች ሥራዎች
(2ዜ.መ. 8፥1-18)
10ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት ሁለቱን ቤቶች የሠራበት ሃያ ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥ 11ንጉሡ ሰሎሞን በገሊላ ምድር ያሉትን ሃያ ከተሞች ለኪራም ሰጠው። የጢሮስም ንጉሥ ኪራም የሚሻውን ያህል የዝግባና የጥድ እንጨት የሚሻውንም ያህል ወርቅ ሁሉ ለሰሎሞን ሰጥቶት ነበር። 12ኪራምም ሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ያይ ዘንድ ከጢሮስ ወጣ፤ ደስም አላሰኙትም። 13እርሱም “ወንድሜ ሆይ! የሰጠኸኝ እነዚህ ከተሞች ምንድር ናቸው?” አለ። እስከ ዛሬም ድረስ የከቡል አገር ተብለው ተጠሩ። 14ኪራምም መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ ለንጉሡ ላከ።
15ንጉሡም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤትና የራሱን ቤት፥ ሚሎንም፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር፥ ሐጾርንም፥ መጊዶንም፥ ጌዝርንም ይሠራ ዘንድ ገባሮችን መልምሎ ነበር። 16የግብጽም ንጉሥ ፈርዖን ወጥቶ ጌዝርን ይዞ ነበር፤ በእሳትም አቃጥሎ ነበር፤ በከተማም የኖሩትን ከነዓናውያን ገድሎ ነበር፤ ለልጁም ለሰሎሞን ሚስት ትሎት አድርጎ ሰጥቶአት ነበር። 17ሰሎሞንም ጌዝርን፥ የታችኛውንም ቤት ሖሮን፥ 18ባዕላትንም፥ በምድረ በዳም አገር ያለችውን ተድሞርን፥ 19ለሰሎሞንም የነበሩትን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ፥ የሠረገላውንም ከተሞች፥ የፈረሰኞችንም ከተሞች፥ በኢየሩሳሌምም በሊባኖስም በመንግሥቱም ምድር ሁሉ ሰሎሞን ይሠራ ዘንድ የወደደውን ሁሉ ሠራ። 20ከእስራኤልም ልጆች ዘንድ ያልነበሩትን ከአሞራውያንና ከኬጢያውያን፥ ከፌርዛውያን፥ ከሒዋውያንና ከኢያቡሳውያን የቀሩትን፥ 21የእስራኤልም ልጆች ያጠፉአቸው ዘንድ ያልቻሉትን፥ በኋላቸው የቀሩትን ልጆቻቸውን፥ ሰሎሞን እስከ ዛሬ ድረስ ገባሮች አድርጎ መለመላቸው። 22ሰሎሞንም ከእስራኤል ልጆች ማንንም ባሪያ አላደረገም፤ እነርሱ ግን ሰልፈኞች ሎሌዎችም፥ መሳፍንትም፥ አለቆችም፥ የሠረገሎችና የፈረሶች ባልደራሶች ነበሩ።
23ሰሎሞንም በሚሠራው ሥራ ላይ ሠራተኛውን ሕዝብ የሚያዝዙ አለቆች አምስት መቶ አምሳ ነበሩ።
24የፈርዖንም ልጅ ከዳዊት ከተማ ሰሎሞን ወደ ሠራላት ወደ ቤትዋ ወጣች፤ በዚያን ጊዜም ሚሎን ሠራ።
25ሰሎሞንም በየዓመቱ ሦስት ጊዜ የሚቃጠለውንና የደኅንነቱን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በሠራው መሠዊያ ላይ ያሳርግ ነበር፤ በእግዚአብሔር ፊት ባለው መሠዊያ ላይ ዕጣን ያሳርግ ነበር፤ ቤቱንም ጨረሰ።
26ንጉሡም ሰሎሞን በኤዶምያስ ምድር በኤርትራ ባሕር ዳር በኤሎት አጠገብ ባለችው በዔጽዮንጋብር መርከቦች ሠራ። 27ኪራምም በእነዚያ መርከቦች ከሰሎሞን ባሪያዎች ጋር የባሕሩን ነገር የሚያውቁ መርከበኞች ባሪያዎቹን ሰደደ። 28ወደ ኦፊርም መጡ፤ ከዚያም አራት መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ ወሰዱ፤ ወደ ንጉሡም ወደ ሰሎሞን ይዘው መጡ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 9: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ