አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 8
8
የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ቤተ መቅደስ መግባት
(2ዜ.መ. 5፥2—6፥2)
1ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ያወጡ ዘንድ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና የነገድ አለቆችን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች የአባቶቻቸውን ቤቶች መሳፍንት፥ ንጉሡ ሰሎሞን ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰባቸው። 2የእስራኤልም ሰዎች ኤታኒም በሚባል በሰባተኛው ወር በበዓሉ ጊዜ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ተከማቹ። 3የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ፤ ካህናቱም ታቦቱን አነሡ። 4የእግዚአብሔርንም ታቦት፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ በድንኳኑም ውስጥ የነበረውን የተቀደሰውን ዕቃ ሁሉ አመጡ፤ እነዚህንም ሁሉ ካህናቱና ሌዋውያኑ አመጡ። 5ንጉሡም ሰሎሞን ከእርሱም ጋር የተሰበሰቡ የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ከእርሱ ጋር በታቦቱ ፊት ሆነው፥ ከብዛታቸው የተነሣ የማይቈጠሩትንና የማይመጠኑትን በጎችና በሬዎች ይሠዉ ነበር። 6ካህናቱም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት በቤቱ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች ወደ ነበረው ወደ ስፍራው አመጡት። 7ኪሩቤልም በታቦቱ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ነበር፤ ኪሩቤልም ታቦቱንና መሎጊያዎቹን በስተላይ በኩል ሸፍነው ነበር። 8መሎጊያዎቹም ረጃጅሞች ነበሩ፤ በቅድስተ ቅዱሳን ፊት ከመቅደሱ ውስጥ ጫፎቻቸው ይታዩ ነበር፤ በውጭ ያለ ግን አያያቸውም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ። 9በታቦቱም ውስጥ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ፥ ሙሴ በኮሬብ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች በቀር ምንም አልነበረበትም። 10ካህናቱም ከመቅደሱ በመጡ ጊዜ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው። 11የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶ ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሣ ለማገልገል ይቆሙ ዘንድ አልቻሉም።
12ሰሎሞንም “እግዚአብሔር ‘በጨለማው ውስጥ እኖራለሁ፤’ ብሎአል፤ 13እኔም ለዘላለም የምትኖርበት ማደሪያ ቤት በእውነት ሠራሁልህ፤” አለ።
ሰሎሞን ለሕዝቡ ያደረገው ንግግር
(2ዜ.መ. 6፥3-11)
14ንጉሡም ፊቱን ዘወር አድርጎ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መረቀ፤ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ቆመው ነበር። 15-16እርሱም አለ “‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብጽ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ ስሜ በዚያ ይሆን ዘንድ፥ በእርስዋም ቤት ይሠራልኝ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከተማ አልመረጥሁም፤ አሁን ግን ስሜ በዚያ ይሆን ዘንድ ኢየሩሳሌምን መርጫለሁ፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ይሆን ዘንድ ዳዊትን መርጫለሁ፤’ ብሎ ለአባቴ ለዳዊት በአፉ የተናገረ፥ በእጁም የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። 17አባቴም ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ይሠራ ዘንድ በልቡ አሰበ። 18እግዚአብሔርም አባቴን ዳዊትን ‘ለስሜ ቤት ትሠራ ዘንድ በልብህ አስበሃልና ይህን በልብህ ማሰብህ መልካም አደረግህ። 19ነገር ግን ከወገብህ የሚወጣው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል እንጂ ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም፤’ አለው። 20እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል አጸና፤ እግዚአብሔርም ተስፋ እንደ ሰጠ በአባቴ በዳዊት ፋንታ ተነሣሁ፤ በእስራኤልም ዙፋን ላይ ተቀመጥሁ፤ ለእስራኤልም አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ሠራሁ። 21ከግብጽም ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ላለበት ታቦት ስፍራ በዚያ አደረግሁለት።”
ሰሎሞን ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው ጸሎት
(2ዜ.መ. 6፥12-42)
22የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ እያዩ ሰሎሞን በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆሞ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘረጋ። 23እንዲህም አለ “የእስራኤል አምላክ አቤቱ! በላይ በሰማይ በታችም በምድር አንተን የሚመስል አምላክ የለም፤ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ለሚሄዱ ባሪያዎችህ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ 24ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ የጠበቅህ፤ በአፍህ ተናገርህ፤ እንደ ዛሬው ቀንም በእጅህ ፈጸምኸው። 25አሁንም የእስራኤል አምላክ አቤቱ! ‘አንተ በፊቴ እንደ ሄድህ ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው በፊቴ አታጣም፤’ ብለህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ ጠብቅ። 26አሁንም፥ የእስራኤል አምላክ ሆይ! ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የተናገርኸው ቃል፥ እባክህ፥ ይጽና።
27“በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ! 28ነገር ግን፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ! ወደ ባሪያህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፤ ዛሬም ባሪያህ በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጥሪውን ስማ፤ 29ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ ‘በዚያ ስሜ ይሆናል፤’ ወዳልኸው ስፍራ ወደዚህ ቤት ዐይኖችህ ሌሊትና ቀን የተገለጡ ይሁኑ። 30ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።
31“ሰው ባልንጀራውን ቢበድል፥ በላዩም መሐላ ቢጫን፥ እርሱም መጥቶ በዚህ ቤት በመሠዊያህ ፊት ቢምል፥ 32በሰማይ ስማ፤ አድርግም፤ በባሪያዎችህም ላይ ዳኛ ሁን፤ በበደለኛውም ላይ ፍረድ፤ መንገዱንም በራሱ ላይ መልስበት፤ ንጹሑን አጽደቀው፤ እንደ ጽድቁም ክፈለው።
33“ሕዝብህ እስራኤል አንተን ስለ በደሉ በጠላቶቻቸው ፊት ድል በተመቱ ጊዜ፥ ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ በዚህም ቤት ቢጸልዩና ቢለምኑህ፥ 34አንተ በሰማይ ስማ፤ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ምድር መልሳቸው።
35“አንተን ስለ በደሉ ሰማይ በተዘጋ ጊዜ፥ ዝናብም ባልዘነበ ጊዜ፥ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ ባስጨነቅሃቸውም ጊዜ ከኀጢአታቸው ቢመለሱ፥ 36አንተ በሰማይ ስማ፤ የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ በማሳየት የባሪያዎችህንና የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለሕዝብህም ርስት አድርገህ ለሰጠሃት ምድር ዝናብ ስጥ።
37“በምድር ላይ ራብ፥ ወይም ቸነፈር፥ ወይም ዋግ፥ ወይም አረማሞ፥ ወይም አንበጣ፥ ወይም ኩብኩባ ቢሆን፥ የሕዝብህም ጠላት የአገሩን ቀበሌዎች ከብቦ ቢያስጨንቃቸው፥ መቅሠፍትና ደዌ ሁሉ ቢሆን፥ 38ማናቸውም ሰው የልቡን ሕመም አውቆ ጸሎትና ልመና ቢጸልይ፥ እጆቹንም ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ፥ 39-40ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ይፈሩህ ዘንድ፥ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ይቅርም በል፤ አንተ ብቻ የሰውን ልጆች ሁሉ ልብ ታውቃለህና፥ ልቡን ለምታውቀው ሰው ሁሉ እንደ መንገዱ ሁሉ መጠን ክፈለውና ስጠው።
41-42“ክከሕዝብህም ከእስራኤል ወገን ያልሆነ እንግዳ ታላቁን ስምህን፥ ብርቱይቱንም እጅህን፥ የተዘረጋውንም ክንድህን ሰምቶ ስለ ስምህ ከሩቅ አገር በመጣ ጊዜ፥ መጥቶ ወደዚህ ቤት በጸለየ ጊዜ፥ 43አንተ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስምህን ያውቁ ዘንድ እንደ ሕዝብህም እንደ እስራኤል ይፈሩህ ዘንድ፥ በዚህም በሠራሁት ቤት ስምህ እንደተጠራ ያውቁ ዘንድ፥ እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ።
44“ሕዝብህም ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ቢወጡ፥ አንተም ወደ መረጥሃት ከተማ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤት ለእግዚአብሔር ቢጸልዩ፥ 45ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ ስማ፤ ፍርድንም አድርግላቸው።
46“የማይበድልም ሰው የለምና አንተን ቢበድሉ፥ ተቆጥተህም ለጠላቶቻቸው አሳልፈህ ብትሰጣቸው፥ ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነ ወደ ጠላቶች አገር ቢማረኩም፥ 47በተማረኩበትም አገር ሆነው በልባቸው ንስሓ ቢገቡ፥ በማራኪዎቹም አገር ሳሉ ተመልሰው ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለንማል፤ ክፉንም አድርገናል፤’ ብለው ቢለምኑህ፥ 48በማረኩአቸው በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃት ወደ ምድራቸው ወደ መረጥሃትም ከተማ ለስምህም ወደ ሠራሁት ቤት ቢጸልዩ፥ 49ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ፍርድንም አድርግላቸው፤ 50አንተንም የበደሉህን ሕዝብህን፥ በአንተም ላይ ያደረጉትን በደላቸውን ሁሉ ይቅር በል፤ ይራሩላቸውም ዘንድ በማረኩአቸው ፊት ምሕረት ስጣቸው፤ 51ከግብጽ ምድር ከብረት እቶን ውስጥ ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸውና። 52በጠሩህ ጊዜ ሁሉ ትሰማቸው ዘንድ ለባሪያህና ለሕዝብህ ለእስራኤል ልመና ዐይኖችህ የተገለጡ ይሁኑ። 53ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ! አባቶቻችንን ከግብጽ ባወጣህ ጊዜ፥ በባሪያህ በሙሴ አማካይነት እንደ ተናገርህ ርስት ይሆኑህ ዘንድ ከምድር አሕዛብ ሁሉ ለይተሃቸዋልና።”
የሰሎሞን የመጨረሻ ጸሎት
54ሰሎሞንም ይህችን ጸሎትና ልመና ሁሉ ለእግዚአብሔር ጸልዮ በፈጸመ ጊዜ፥ በጕልበቱ ተንበርክኮ እጁንም ወደ ሰማይ ዘርግቶ ነበርና ከእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ተነሣ። 55ቆሞም የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ በታላቅ ድምጽ ሲመርቅ እንዲህ አለ 56“እንደ ተናገረው ተስፋ ሁሉ ለሕዝቡ ለእስራኤል ዕረፍትን የሰጠ እግዚአብሔር ይመስገን! በባሪያው በሙሴ ከሰጠው ከመልካም ተስፋ ሁሉ አንድ ቃል አልወደቀም። 57አምላካችን እግዚአብሔር ከአባቶቻችን ጋር እንደ ነበረ ከእኛ ጋር ይሁን! አይተወን! አይጣለንም! 58በመንገዱም ሁሉ እንሄድ ዘንድ፥ ለአባቶቻችንም ያዘዛትን ሥርዐትና ፍርድ ትእዛዙንም እንጠብቅ ዘንድ፥ ልባችንን ወደ እርሱ ያዘነብል ዘንድ። 59ለባሪያውና ለሕዝቡ ለእስራኤል በየዕለቱ ፍርድን ያደርግ ዘንድ ይህች በእግዚአብሔር ፊት የለመንኋት ቃል በቀንና በሌሊት ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር የቀረበች ትሁን! 60የምድር አሕዛብ ሁሉ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ፥ ከእርሱም በቀር ሌላ እንደሌለ ያውቅ ዘንድ። 61እንደ ዛሬው ቀን በሥርዐቱ ትሄዱ ዘንድ፥ ትእዛዙንም ትጠብቁ ዘንድ፥ ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጋር ልባችሁ ፍጹም ይሁን።”
የቤተ መቅደሱ መመረቅ
(2ዜ.መ. 7፥4-10)
62ንጉሡም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት ሠዉ። 63ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ለደኅንነት መሥዋዕት ሃያ ሁለት ሺህ በሬዎችና መቶ ሃያ ሺህ በጎች አቀረበ። ንጉሡና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲሁ የእግዚአብሔርን ቤት ቀደሱ። 64በእግዚአብሔር ፊት ያለው የናሱ መሠዊያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቁርባን የደኅንነቱንም መሥዋዕት ስብ ይይዝ ዘንድ ታናሽ ስለ ነበረ፥ በዚያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቁርባን የደኅንነቱንም መሥዋዕት ስብ አሳርጎአልና በእግዚአብሔር ቤት ፊት የነበረውን የአደባባዩ መካከል ንጉሡ በዚያ ቀን ቀደሰ። 65በዚያም ዘመን ሰሎሞን ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ፥ ከሐማት መግቢያ ጀምሮ እስከ ግብጽ ወንዝ ድረስ ያለው ታላቅ ጉባኤ፥ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀን በዓሉን አደረጉ። 66በስምንተኛውም ቀን ሕዝቡን አሰናበተ፤ እነርሱም ንጉሡን መረቁ፤ እግዚአብሔርም ለባሪያው ለዳዊትና ለሕዝቡ ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት ሁሉ በልባቸው ተደስተው ሐሤትም አድርገው ወደ ስፍራቸው ሄዱ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 8: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ