የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 4:20-34

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 4:20-34 አማ54

ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር። ሰሎሞንም ከወንዙ ጀምሮ እስከ ግብጽ ዳርቻ እስከ ፍልስጥኤም ድረስ በመንግሥታት ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር፤ ግብርም ያመጡለት ነበር፤ በዕድሜውም ሙሉ ለሰሎሞን ይገዙ ነበር። ለሰሎሞንም ለቀን ለቀኑ ቀለብ የሚሆን ሠላሳ ኮር መልካም ዱቄትና ስድሳ ኮር መናኛ ድቄት፥ ከዋላና ከሚዳቋ ከበረሃ ፍየልና ከሰቡ ወፎች በቀር ዐሥር ፍሪዳዎች ሃያም የተሰማሩ በሬዎች አንድ መቶም በጎች ነበረ። ከወንዙ ወዲህ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ከወንዙም ወዲህ ባለው አገር ሁሉ ላይ ከቲፍሳ ጀምሮ እስከ ጋዛ ድረስ ነግሦ ነበር፤ በዙሪያውም ባለ በሁሉ ወገን ሰላም ሆኖለት ነበር። በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እስራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር። ለሰሎሞንም በአርባ ሺህ ጋጥ የሚገቡ የሠረገላ ፈረሶች ዐሥራ ሁለትም ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት። እነዚያም ሹሞች እያንዳንዱ በየወሩ ንጉሡን ሰሎሞንንና ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ማዕድ የሚቀርቡትን ሁሉ ይቀልቡ ነበር፤ ምንም አያጎድሉም ነበር። እያንዳንዱም እንደ ደንቡ ለፈረሶቹና ለሰጋር በቅሎች ገብስና ጭድ ወደ ስፍራቸው ያመጡ ነበር። እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው። የሰሎሞንም ጥበብ በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብጽ ጥበብ ሁሉ በለጠ። ከሰውም ሁሉ ይልቅ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታንና ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ከደራልም ይልቅ ጥበበኛ ነበረ። በዙሪያውም ባሉ አሕዛብ ሁሉ ዝናው ወጣ። እርሱም ሦስት ሺህ ምሳሌዎች ተናገረ፤ መኃልዩም ሺህ አምስት ነበረ። ስለ ዛፍም ከሊባኖስ ዝግባ ጀምሮ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው እስከ ሂሶጵ ድረስ ይናገር ነበር፤ ደግሞም ስለ አውሬዎችና ስለ ወፎች ሰለተንቀሳቃሾችና ስለ ዓሣዎች ይናገር ነበር። ከአሕዛብም ሁሉ፥ ጥበቡንም ሰምተው ከነበሩ ከምድር ነገሥታ ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ሰዎች ይመጡ ነበር።