አክዓብም ኤልያስን ባየው ጊዜ “እስራኤልን የምትገለባብጥ አንተ ነህን?” አለው። ኤልያስም “እስራኤልን የምትገለባብጡ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ በኣሊምን የተከተላችሁ፥ አንተና የአባትህ ቤት ናችሁ እንጂ እኔ አይደለሁም። አሁንም ልከህ እስራኤልን ሁሉ፥ በኤልዛቤልም ማዕድ የሚበሉትን አራት መቶ አምሳ የበኣልን ነቢያት፥ አራት መቶም የማምለኪያ ዐፀድን ነቢያት ወደ እኔ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰብስብ፤” አለ። አክዓብም ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ ልኮ ነቢያቱን ሁሉ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰበሰበ። ኤልያስም ወደ ሕዝቡ ሁሉ ቀርቦ “እስከ መቼ ድረስ በሁለት አሳብ ታነክሳላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤ በኣል ግን አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤” አለ። ሕዝቡም አንዲት ቃል አልመለሱለትም። ኤልያስም ሕዝቡን አለ “ከእግዚአብሔር ነቢያት እኔ ብቻ ቀርቻለሁ፤ የበኣል ነቢያት ግን አራት መቶ አምሳ ሰዎች ናቸው። ሁለት ወይፈኖች ይሰጡን፤ እነርሱም አንድ ወይፈን ይምረጡ፤ በየብልቱም ይቁረጡት፤ በእንጨትም ላይ ያኑሩት፤ በበታቹም እሳት አይጨምሩ፤ እኔም ሁለተኛውን ወይፈን አዘጋጃለሁ፤ በእንጨቱም ላይ አኖረዋለሁ፤ በበታቹም እሳት አልጨምርም። እናንተም የአምላካችሁን ስም ጥሩ፤ እኔም የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶም በእሳት የሚመልስ አምላክ፥ እርሱ አምላክ ይሁን።” ሕዝቡም ሁሉ “ይህ ነገር መልካም ነው፤” ብለው መለሱ። ኤልያስም የበኣልን ነቢያት “እናንተ ብዙዎች ናችሁና አስቀድማችሁ አንድ ወይፈን ምረጡና አዘጋጁ፤ የአምላካችሁንም ስም ጥሩ፤ በበታቹም እሳት አትጨምሩ፤” አላቸው። ወይፈኑንም ወስደው አዘጋጁ፤ ከጥዋትም እስከ ቀትር ድረስ “በኣል ሆይ! ስማን፤” እያሉ የበኣልን ስም ጠሩ። ድምፅም አልነበረም፤ የሚመልስም አልነበረም፤ በሠሩትም መሠዊያ ዙሪያ እያነከሱ ያሸበሽቡ ነበር። በቀትርም ጊዜ ኤልያስ “አምላክ ነውና በታላቅ ቃል ጩኹ፤ ምናልባት አሳብ ይዞታል፤ ወይም ፈቀቅ ብሎአል፤ ወይም ወደ መንገድ ሄዶአል፤ ወይም ተኝቶ እንደ ሆነ መቀስቀስ ያስፈልገዋል፤” እያለ አላገጠባቸው። በታላቅም ቃል ይጮኹ፥ እንደ ልማዳቸውም ደማቸው እስኪፈስስ ድረስ ገላቸውን በካራና በጩቤ ይብዋጭሩ ነበር። ቀትርም ካለፈ በኋላ መሥዋዕተ ሠርክ እስኪደርስ ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ ድምፅም አልነበረም፤ የሚመልስና የሚያደምጥም አልነበረም። ኤልያስም ሕዝቡን ሁሉ “ወደ እኔ ቅረቡ፤” አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ። ፈርሶ የነበረውንም የእግዚአብሔርን መሠዊያ አበጀ። ኤልያስም “ስምህ እስራኤል ይሆናል፤” የሚል የእግዚአብሔር ቃል እንደ ደረሰለት እንደ ያዕቆብ ልጆች ነገድ ቁጥር ዐሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ወሰደ። ከድንጋዮችም ለእግዚአብሔር ስም መሠዊያ ሠራ፤ በመሠዊያውም ዙሪያ ሁለት መስፈሪያ እህል የሚይዝ ጕድጓድ ቆፈረ። እንጨቱንም በተርታ አደረገ፤ ወይፈኑንም በብልት በብልቱ ቆረጠ፤ በእንጨቱም ላይ አኖረና “አራት ጋን ውሃ ሙሉ በሚቃጠለው መሥዋዕትና በእንጨቱ ላይ አፍስሱ፤” አለ። ደግሞም “ድገሙ” አለ፤ እነርሱም ደገሙ። እርሱም “ሦስተኛ አድርጉ፤” አለ፤ ሦስተኛም አደረጉ። ውሃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ደግሞም ጕድጓዱን ውሃ ሞላው። የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ ነቢዩ ኤልያስ ቀርቦ “አቤቱ፥ የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ! አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ፥ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ፥ ይህንም ሁሉ በቃልህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይገለጥ። አቤቱ፥ አንተ አምላክ እንደ ሆንህ፥ ልባቸውንም ደግሞ እንደ መለስህ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፤ አቤቱ፥ ስማኝ፤” አለ። የእግዚአብሔርም እሳት ወደቀች፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕቱንም፥ እንጨቱንም፥ ድንጋዮቹንም፥ አፈሩንም በላች፤ በጕድጓዱም ውስጥ ያለውን ውሃ ላሰች። ሕዝቡም ሁሉ ያንን ባዩ ጊዜ በግምባራቸው ተደፍተው “እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው! እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው!” አሉ።
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 18 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 18:17-39
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች