አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 17
17
ኤልያስ የድርቅ ዘመን እንደሚመጣ መናገሩ
1በገለዓድ ቴስቢ የነበረው ቴስብያዊው ኤልያስ አክዓብን “በፊቱ የቆምሁት የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! ከአፌ ቃል በቀር በእነዚህ ዓመታት ጠልና ዝናብ አይሆንም፤” አለው። 2የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ለእርሱ መጣለት 3“ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፤ በዮርዳኖስም ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ተሸሸግ። 4ከወንዙም ትጠጣለህ፤ ቍራዎችም በዚያ ይመግቡህ ዘንድ አዝዣለሁ።” 5ሄደም፤ እንደ እግዚአብሔር ቃልም አደረገ። ሄዶም በዮርዳኖስ ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ተቀመጠ። 6ቍራዎችም በየጥዋትና በየማታው እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር፤ ከወንዙም ይጠጣ ነበር። 7ከብዙ ቀንም በኋላ በምድር ላይ ዝናብ አልነበረምና ወንዙ ደረቀ።
ኤልያስና በሰራፕታ ትኖር የነበረች መበለት
8የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እርሱ መጣ። 9“ተነሥተህም በሲዶና አጠገብ ወዳለችው ወደ ሰራፕታ ሂድ፤ በዚያም ተቀመጥ፤ እነሆም፥ ትመግብህ ዘንድ አንዲት ባልቴት አዝዣለሁ፤” 10ተነሥቶም ወደ ሰራፕታ ሄደ፤ ወደ ከተማይቱም በር በደረሰ ጊዜ አንዲት ባልቴት በዚያ እንጨት ትለቅም ነበር፤ እርሱም ጠርቶ “የምጠጣው ጥቂት ውሃ በጽዋ ታመጭልኝ ዘንድ እለምንሻለሁ፤” አላት። 11ውሃም ልታመጣለት በሄደች ጊዜ ወደ እርስዋ ጠርቶ “ቍራሽ እንጀራ በእጅሽ ይዘሽ ትመጭ ዘንድ እለምንሻለሁ፤” አላት። 12እርስዋም “አምላክህ ሕያው እግዚአብሔርን! በማድጋ ካለው ከእፍኝ ዱቄት፥ በማሰሮም ካለው ከጥቂት ዘይት በቀር እንጀራ የለኝም፤ እነሆም፥ ገብቼ ለእኔና ለልጄ እጋግረው ዘንድ በልተነውም እንሞት ዘንድ ጥቂት እንጨት እሰበስባለሁ፤” አለች። 13ኤልያስም አላት “አትፍሪ፤ ይልቅስ ሄደሽ እንዳልሺው አድርጊ፤ አስቀድመሽ ግን ከዱቄቱ ለእኔ ታናሽ እንጎቻ አድርገሽ አምጭልኝ፤ ከዚያም በኋላ ለአንቺና ለልጅሽ አድርጊ፤ 14የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና ‘በምድር ላይ እግዚአብሔር ዝናብ እስከሚሰጥበት ቀን ድረስ፥ ዱቄቱ ከማድጋ አይጨረስም፤ ዘይቱም ከማሰሮው አይጎድልም።’” 15እርስዋም ሄዳ እንደ ኤልያስ ቃል አደረገች፤ እርስዋና እርሱ ቤትዋም ብዙ ቀን በሉ። 16በኤልያስም አማካይነት እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ዱቄቱ ከማድጋው አልተጨረሰም፤ ዘይቱም ከማሰሮው አልጎደለም።
17ከዚያም በኋላ የባለቤቲቱ ልጅ ታመመ፤ ትንፋሹም እስኪታጣ ድረስ ደዌው እጅግ ከባድ ነበረ። 18እርስዋም ኤልያስን “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ኀጢአቴንስ ታሳስብ ዘንድ፥ ልጄንስ ትገድል ዘንድ ወደ እኔ መጥተሃልን?” አለችው። 19ኤልያስም “ልጅሽን ስጪኝ፤” አላት። ከብብትዋም ወስዶ ተቀምጦበት ወደ ነበረው ሰገነት አወጣው፤ በአልጋውም ላይ አጋደመው። 20ወደ እግዚአብሔርም “አቤቱ አምላኬ ሆይ! ልጅዋን በመግደልህ ይህችን ትቀልበኝ የነበረቺቱን ባልቴት እንዲህ ደግሞ አስጨነቅኻትን?” ብሎ ጮኸ። 21በብላቴናውም ላይ ሦስት ጊዜ ተዘረጋበት፤ ወደ እግዚአብሔርም “አቤቱ አምላኬ ሆይ! የዚህ ብላቴና ነፍስ ወደ እርሱ ትመለስ ዘንድ እለምንሃለሁ፤” ብሎ ጮኸ። 22እግዚአብሔርም የኤልያስን ቃል ሰማ፤ የብላቴናውም ነፍስ ወደ እርሱ ተመለሰች፤ እርሱም ዳነ። 23ኤልያስም ብላቴናውን ይዞ ከሰገነቱ ወደ ቤት አወረደው፤ ኤልያስም “እነሆ፥ ልጅሽ በሕይወት ይኖራል፤” ብሎ ለእናቱ ሰጣት። 24ሴቲቱም ኤልያስን “የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንህ፥ የእግዚአብሔርም ቃል በአፍህ እውነት እንደ ሆነ አሁን አወቅሁ፤” አለችው።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 17: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ