አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 14
14
የኢዮርብዓም ወንድ ልጅ መሞት
1በዚያም ወራት የኢዮርብዓም ልጅ አብያ ታመመ። 2ኢዮርብዓምም ሚስቱን “ተነሺ፤ የኢዮርብዓምም ሚስት እንደ ሆንሽ እንዳትታወቂ ልብስሽን ለውጪና ወደ ሴሎ ሂጂ፤ እነሆ፥ በዚህ ሕዝብ ላይ እንድነግሥ የነገረኝ ነቢዩ አኪያ በዚያ አለ። 3በእጅሽም ዐሥር እንጀራና እንጎቻዎች አንድም ምንቸት ማር ይዘሽ ወደ እርሱ ሂጂ፤ በልጁም የሚሆነውን ይነግርሻል፤” አላት። 4የኢዮርብዓምም ሚስት እንዲሁ አደረገች፤ ተነሥታም ወደ ሴሎ ሄደች፤ ወደ አኪያም ቤት መጣች። አኪያም ስለ መሸምገሉ ዐይኖቹ ፈዝዘው ነበርና ማየት አልቻለም። 5እግዚአብሔርም አኪያን “እነሆ፥ ስለ ታመመው ልጅዋ ትጠይቅህ ዘንድ የኢዮርብዓም ሚስት ትመጣለች፤ ሌላ ሴትም መስላ ተሰውራለችና በገባች ጊዜ እንዲህና እንዲህ በላት፤” አለው።
6እርስዋም በደጅ ስትገባ አኪያ የእግርዋን ኮቴ ሰማ፤ እንዲህም አለ “የኢዮርብዓም ሚስት ሆይ! ግቢ፤ ስለ ምንስ ሌላ ሴት መሰልሽ? እኔም ብርቱ ወሬ ይዤ ተልኬልሻለሁ። 7ሂጂ፤ ለኢዮርብዓምም እንዲህ በዪው ‘የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከሕዝብ መካከል ለይቼ ከፍ አድርጌህ ነበር፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ አድርጌህ ነበር፤ 8ከዳዊትም ቤት መንግሥቱን ቀድጄ ሰጥቼህ ነበር፤ ነገር ግን በፍጹም ልቡ እንደ ተከተለኝ፥ በፊቴም ቅን ነገር ብቻ እንዳደረገ፥ ትእዛዜንም እንደ ጠበቀ እንደ ባሪያዬ እንደ ዳዊት አልሆንህም። 9ከአንተም አስቀድመው ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ክፉ ሠራህ፤ ታስቆጣኝም ዘንድ ሄደህ ሌሎችን አማልክትና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎች አደረግህ፤ ወደ ኋላህም ጣልኸኝ። 10ስለዚህ፥ እነሆ፥ በኢዮርብዓም ቤት ላይ መከራ አመጣለሁ፤ ከኢዮርብአምም በእስራኤል ዘንድ የታሰረውንና የተለቀቀውን ወንድ ሁሉ እቆርጣለሁ፤ ሰውም ፋንድያን እስኪጠፋ ድረስ እንደሚጠርግ እኔ የኢዮርብዓምን ቤት ፈጽሜ እጠርጋለሁ። 11ከኢዮርብዓምም ወገን በከተማይቱ ውስጥ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።’ 12“እንግዲህ ተነሥተሽ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እግርሽም ወደ ከተማ በገባ ጊዜ ልጁ ይሞታል። 13እስራኤልም ሁሉ ያለቅሱለታል፤ ይቀብሩትማል፤ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ በኢዮርብዓም ቤት በዚህ ልጅ መልካም ነገር ተገኝቶበታልና ከኢዮርብዓም እርሱ ብቻ ይቀበራል። 14እግዚአብሔርም ደግሞ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ያስነሣል፤ እርሱም በዚያ ዘመን የኢዮርብዓምን ቤት ያጠፋል። 15በዚያ ጊዜም ሸምበቆ በውሃ ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ እግዚአብሔር እንዲሁ እስራኤልን ይመታል፤ እግዚአብሔርንም ያስቆጡ ዘንድ የማምለኪያ ዐፀድ ተክለዋልና ለአባቶቻቸው ከሰጣቸው ከዚች ከመልካሚቱ ምድር እስራኤልን ይነቅላል፤ በወንዙም ማዶ ይበትናቸዋል። 16ስለ በደለውና እስራኤልንም ስላሳተበት ስለ ኢዮርብዓም ኀጢአት እስራኤልን ይጥላል።”
17የኢዮርብዓምም ሚስት ተነሥታ ሄደች፤ ወደ ቴርሳ መጣች፤ ወደ ቤቱም መድረክ በገባች ጊዜ ልጁ ሞተ። 18በባሪያውም በነቢዩ በአኪያ እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል እስራኤል ሁሉ ቀበሩት፤ አለቀሱለትም።
የኢዮርብዓም መሞት
19የቀረውም የኢዮርብዓም ነገር፥ እንዴት እንደ ተዋጋ፥ እንዴትም እንደ ነገሠ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 20ኢዮርብዓምም የነገሠበት ዘመን ሃያ ሁለት ዓመት ነበረ፤ ከአባቶቹም ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ናዳብ በፋንታው ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ ሮብዓም
(2ዜ.መ. 11፥5—12፥15)
21የሰሎሞንም ልጅ ሮብዓም በይሁዳ ነገሠ፤ ሮብዓምም ንጉሥ በሆነ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስሙን ያኖርባት ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም ዐሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ የእናቱም ስም ናዕማ ነበረ፤ እርስዋም አሞናዊት ነበረች። 22ይሁዳም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ፤ አባቶቻቸውም ከሠሩት ሁሉ ይልቅ አብዝተው በሠሩት ኀጢአት አስቆጡት። 23እነርሱም ደግሞ ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ፥ ቅጠሉ ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች መስገጃዎችንና ሐውልቶችን የማምለኪያ ዐፀዶችንም ለራሳቸው ሠሩ። 24በምድርም ውስጥ ሰዶማውያን ነበሩ፤ ከእራኤልም ልጆች ፊት እግዚአብሔር ያሳደዳቸውን የአሕዛብን ርኵሰት ሁሉ ያደርጉ ነበር። 25ሮብዓምም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ መጣ። 26የእግዚአብሔርም ቤተ መዛግብትንና የንጉሥ ቤተ መዛግብትን ወሰደ፤ ሁሉንም ወሰደ፤ ሰሎሞንም የሠራውን የወርቁን ጋሻ ሁሉ ወሰደ። 27ንጉሡም ሮብዓም በፋንታው የናስ ጋሾችን ሠራ፤ የንጉሥንም ቤት ደጅ በሚጠብቁ በዘበኞች አለቆች እጅ አኖራቸው። 28ንጉሡም ዘወትር ወደ እግዚአብሔር ቤት ሲገባ ዘበኞች ይሸከሙአቸው ነበር፤ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸው ነበር።
29የቀረውም የሮብዓም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 30በዘመኑም ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ሰልፍ ነበረ። 31ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። ልጁም አብያም በፋንታው ነገሠ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 14: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ