የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 15

15
የይሁዳ ንጉሥ አብያ
(2ዜ.መ. 13፥1—14፥1)
1የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያም በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ። 2በኢየሩሳሌምም ሦስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም መዓካ የተባለችው የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። 3ከእርሱ አስቀድሞ ባደረገው በአባቱ ኀጢአት ሁሉ ሄደ፤ ልቡም እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም አልነበረም። 4ነገር ግን ልጁን ከእርሱ በኋላ ያስነሣ ዘንድ፥ ኢየሩሳሌምንም ያጸና ዘንድ አምላኩ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት በኢየሩሳሌም መብራት ሰጠው፤ 5ዳዊት በዘመኑ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አድርጎ ነበርና፥ ካዘዘውም ነገር ሁሉ ፈቀቅ አላለም ነበርና። 6በኢዮርብዓምና በሮብዓም ልጅ በአብያም መካከል በዘመኑ ሁሉ ጠብ ነበረ። 7የቀረውም የአብያም ነገር፥ ያደርገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በአብያና በኢዮርብዓም መካከል ሰልፍ ነበረ። 8አብያምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት። ልጁም አሳ በፋንታው ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ አሳ
(2ዜ.መ. 15፥16—16፥6)
9በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም በኻያኛውም ዓመት አሳ በይሁዳ ላይ ነገሠ። 10በኢየሩሳሌምም አርባ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። 11አሳ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። 12ከአገሩም ሰዶማውያንን አስወገደ፤ አባቶቹም ያደረጉትን ጣዖታትን ሁሉ አራቀ። 13በማምለኪያ ዐፀድ ጣዖት ስለሠራች እናቱን መዓካን እቴጌ እንዳትሆን ሻራት፤ ጣዖትዋንም ሰበረው፤ በቄድሮንም ፈፋ አጠገብ አቃጠለው። 14ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉትን መስገጃዎች አላራቀም፤ የአሳ ልብ ግን በዘመኑ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ነበረ። 15አባቱ የቀደሰውንና እርሱም የቀደሰውን ወርቅና ብር ዕቃውንም ወደ እግዚአብሔር ቤት አገባው።
16በአሳና በእስራኤል ንጉሥ በባኦስ መካከል በዘመናቸው ሁሉ ሰልፍ ነበረ። 17የእስራኤልም ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ወጣ፤ ከይሁዳ ንጉሥ ከአሳ ዘንድ ማንም እንዳይወጣ ወደ እርሱም ማንም እንዳይገባ አድርጎ ራማን ሠራ። 18አሳም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሥ ቤት መዛግብት የቀረውን ብርና ወርቅ ሁሉ ወስዶ በባሪያዎቹ እጅ ሰጣቸው፤ ንጉሡም አሳ በደማስቆ ለተቀመጠው ለአዚን ልጅ ለጠብሪሞን ልጅ ለሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ 19“በእኔና በአንተ መካከል በአባቴና በአባትህም መካከል ቃል ኪዳን ጸንቶአል፤ እነሆ፥ ብርና ወርቅ ገጸ በረከት ሰድጄልሃለሁ፤ እርሱ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ ሄደህ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያለህን ቃል ኪዳን አፍርስ፤” ብሎ ሰደደ። 20ቤንሀዳድም ለንጉሡ ለአሳ እሺ አለው፤ የሠራዊቱንም አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ ሰድዶ ዒዮንንና ዳንን፥ አቤልቤት መዓካንና ኪኔሬትን ሁሉ የንፍታሌምንም አገር ሁሉ መታ። 21ባኦስም ያን በሰማ ጊዜ ራማን መሥራት ትቶ በቴርሳ ተቀመጠ። 22ንጉሡም አሳ በይሁዳ ሁሉ ላይ አዋጅ ነገረ፤ ማንም ነጻ አልነበረም፤ ባኦስም የሠራበትን የራማን ድንጋይና እንጨት ወሰዱ፤ ንጉሡም አሳ የብንያምን ጌባንና ምጽጳን ሠራበት።
23የቀረውም የአሳ ነገር ሁሉ፥ ጭከናውም ሁሉ፥ ያደረገውም ሁሉ፥ የሠራቸውም ከተሞች፥ በይሁዳ ነገሥት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ነገር ግን በሸመገለ ጊዜ እግሮቹ ታመሙ። 24አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። ልጁም ኢዮሣፍጥ በፋንታው ነገሠ።
የእስራኤል ንጉሥ ናዳብ
25በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሁለተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ናዳብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በእስራኤልም ላይ ሁለት ዓመት ነገሠ። 26በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፤ በአባቱም መንገድ እስራኤልንም ባሳተበት ኀጢአት ሄደ። 27ከይሳኮርም ቤት የሆነ የአኪያ ልጅ ባኦስ ተማማለበት፤ ናዳብና እስራኤልም ሁሉ ገባቶንን ከብበው ነበርና ባኦስ በፍልስጥኤም አገር ባለው በገባቶን ገደለው። 28በይሁዳ ንጉሥ በአሳ በሦስተኛው ዓመት ባኦስ ናዳብን ገደለው፤ በፋንታውም ነገሠ። 29-30ንጉሥም በሆነ ጊዜ የኢዮርብዓምን ቤት ሁሉ መታ፤ ኢዮርብዓምም ስለ ሠራው ኀጢአት፥ እስራኤልንም ስላሳተበት፥ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን ስላስቆጣበት ማስቆጫ፥ በባሪያው በሴሎናዊው በአኪያ እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል እስኪያጠፋው ድረስ ከኢዮርብዓም አንድ ትንፋሽ ያለው አላስቀረም።
31የቀረውም የናዳብ ነገርና ያደረገው ሁሉ፥ 32በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ
33በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሦስተኛው ዓመት የአኪያ ልጅ ባኦስ በእስራኤል ሁሉ ላይ በቴርሳ ንጉሥ ሆኖ ኻያ አራት ዓመት ነገሠ። 34በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፤ በኢዮርብዓምም መንገድ እስራኤልንም ባሳተበት ኀጢአት ሄደ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ