አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 12

12
በሰሜን የሚኖሩ የእስራኤል ነገዶች ዐመፅ
(2ዜ.መ. 10፥1-19)
1እስራኤል ሁሉ ያነግሡት ዘንድ ወደ ሴኬም መጥተው ነበርና ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ። 2እንዲህም ሆነ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን በሰማ ጊዜ፥ እርሱም ከንጉሡ ከሰሎሞን ፊት ኰብልሎ በግብጽ ተቀምጦ ነበርና፥ በግብጽም ሳለ ልከው ጠርተውት ነበርና 3ኢዮርአብዓምና የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ መጥተው ለሮብዓም 4“አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቃልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን፤” ብለው ተናገሩት። 5እርሱም “ሂዱ፤ በሦስተኛውም ቀን ወደ እኔ ተመለሱ፤” አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ።
6ንጉሡም ሮብዓም “ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው?” ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ። 7እነርሱም “ለዚህ ሕዝብ አሁን ባሪያ ብትሆን ብትገዛላቸውም፥ መልሰህም በገርነት ብትናገራቸው፥ በዘመኑ ሁሉ ባሪያዎች ይሆኑልሃል፤” ብለው ተናገሩት። 8እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ። 9እርሱም “‘አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቃልልልን፤’ ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው?” አላቸው። 10ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች “‘አባትህ ቀንበር አክብዶብናል፤ አንተ ግን አቃልልልን፤’ ለሚሉህ ሕዝብ፥ ‘ታናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች። 11አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችኋል፤ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችኋል፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ፤’ በላቸው፤” ብለው ተናገሩት።
12ንጉሡም “በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ፤” ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ። 13ንጉሡም ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ለሕዝቡ ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው። 14እንደ ብላቴኖችም ምክር “አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፤ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ፤” ብሎ ተናገራቸው። 15እግዚአብሔርም በሴሎናዊው በአኪያ አድርጎ ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረውን ነገር እንዲያጸና ከእግዚአብሔር ዘንድ ተመድቦ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም።
16እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ እንዳልሰማቸው ባዩ ጊዜ ሕዝቡ ለንጉሡ “በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም። እስራኤል ሆይ! ወደ ድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤ ዳዊት ሆይ! አሁን ቤትህን ተመልከት፤” ብለው መለሱለት። እስራኤልም ወደ ድንኳኖቻቸው ሄዱ። 17በይሁዳ ከተሞች በተቀመጡት በእስራኤል ልጆች ላይ ግን ሮብዓም ነገሠባቸው። 18ንጉሡም ሮብዓም አስገባሪውን አዶኒራምን ሰደደ፤ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ደበደቡት፤ ሞተም። ንጉሡም ሮብዓም ፈጥኖ ወደ ሠረገላው ወጣ ወደ ኢየሩሳሌምም ሸሸ። 19እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከዳዊት ቤት ሸፈተ። 20እስራኤልም ሁሉ ኢዮርብዓም እንደ ተመለሰ በሰሙ ጊዜ ልከው ወደ ሸንጎአቸው ጠሩት፤ በእስራኤልም ሁሉ ላይ አነገሡት። ከብቻው ከይሁዳ ነገድ በቀር የዳዊትን ቤት የተከተለ አንድ ሰው አልነበረም።
ሳማያ የተናገረው የትንቢት ቃል
(2ዜ.መ. 11፥1-4)
21ሮብዓምም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ የእስራኤልንም ቤት ወግተው መንግሥቱን ወደ ሰሎሞን ልጅ ወደ ሮብዓም ይመልሱ ዘንድ ከይሁዳ ቤት ሁሉና ከብንያም ነገድ የተመረጡትን አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ሰልፈኞች ሰዎች ሰበሰበ። 22የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሳማያ 23ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓምና ለይሁዳ ለብንያምም ቤት ሁሉ ለቀረውም ሕዝብ ሁሉ 24“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ይህ ነገር ከእኔ ዘንድ ነውና አትውጡ፤ የእስራኤልንም ልጆች ወንድሞቻችሁን አትውጉ፤ እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ይመለስ፤’ ብለህ ንገራቸው፤” ሲል መጣ። የእግዚአብሔርንም ቃል ሰሙ፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል ተመልሰው ሄዱ።
ኢዮርብዓም ፊቱን ከእግዚአብሔር ወደ ሌላ እንደ መለሰ
25ኢዮርብዓምም በተራራማው በኤፍሬም አገር ሴኬምን ሠርቶ በዚያ ተቀመጠ፤ ደግሞም ከዚያ ወጥቶ ጵኒኤልን ሠራ። 26ኢዮርብዓምም በልቡ “አሁን መንግሥቱ ወደ ዳዊት ቤት ይመለሳል። 27ይህ ሕዝብ በእግዚአብሔር ቤት መሥዋዕትን ያቀርብ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ቢወጣ፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ወደ ጌታቸው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓም ይመለሳል፤ እኔንም ይገድሉኛል፤” አለ። 28ንጉሡም ተማከረ፤ ሁለትም የወርቅ ጥጆች አድርጎ “እስራኤል ሆይ! ወደ ኢየሩሳሌም ትወጡ ዘንድ ይበዛባችኋል፤ ከግብጽ ምድር ያወጡህን አማልክቶችህን እይ!” አላቸው። 29አንዱን በቤቴል፥ ሁለተኛውንም በዳን አኖረ። 30ለአንዱ ጥጃ ይሰግድ ዘንድ ሕዝቡ እስከ ዳን ድረስ ይሄድ ነበርና ይህ ኀጢአት ሆነ። 31በኮረብቶቹም ላይ መስገጃዎች ሠራ፤ ከሌዊ ልጆች ካይደሉ ከሕዝብ ሁሉ ካህናትን አደረገ።
በቤቴል የተጀመረው የጣዖት አምልኮ መወገዝ
32በስምንተኛው ወር በዐሥራ አምስተኛውም ቀን በይሁዳ እንደሚደረግ በዓል ያለ በዓል አደረገ፤ በመሠዊያውም ላይ ሠዋ፤ ለሠራቸውም ጥጆች ይሠዋ ዘንድ እንዲሁ በቤቴል አደረገ፤ ለኮረብታ መስገጃዎችም የመረጣቸውን ካህናት በቤቴል አኖራቸው። 33በስምንተኛውም ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን በልቡ ባሰበው ቀን በቤቴል በሠራው መሠዊያ ላይ ሠዋ፤ ለእስራኤልም ልጆች በዓል አደረገላቸው፤ በመሠዊያውም ሠዋ፤ ዕጣንም ዐጠነ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ