አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 11
11
የሰሎሞን ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ
1ንጉሡም ሰሎሞን ከፈርዖን ልጅ ሌላ፥ በሞዓባውያንና በአሞናውያን በኤዶማውያንም በሲዶናውያንና በሒታውያን ሴቶች፥ በብዙ እንግዶች ሴቶች ፍቅር ተነደፈ። 2እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች “አምላኮቻቸውን ትከተሉ ዘንድ ልባችሁን በእውነት ያዘነብላሉና ወደ እነርሱ አትግቡ፤ እነርሱም ወደ እናንተ አይግቡ፤” ካላቸው ከአሕዛብ፥ ከእነዚህ ጋር ሰሎሞን በፍቅር ተጣበቀ። 3ለእርሱም ወይዛዝርት የሆኑ ሰባት መቶ ሚስቶች ሦስት መቶም ቁባቶች ነበሩት፤ ሚስቶቹም ልቡን አዘነበሉት። 4ሰሎሞንም ሲሸመግል ሚስቶቹ ሌሎችን አማልክት ይከተል ዘንድ ልቡን አዘነበሉት፤ የአባቱ የዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም እንደ ነበረ የሰሎሞን ልቡ እንዲሁ አልነበረም። 5ሰሎሞንም የሲዶናውያንን አምላክ አስታሮትን፥ የአሞናውያንንም ርኵሰት ሚልኮምን ተከተለ። 6ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት እግዚአብሔርን በመከተል ፍጹም አልሆነም። 7በዚያን ጊዜም ሰሎሞን ለሞዓብ ርኵሰት ለካሞሽ፥ ለአሞንም ልጆች ርኵሰት ለሞሎክ በኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ባለው ተራራ ላይ መስገጃ ሠራ። 8ለአማልክቶቻቸው ዕጣን ለሚያጥኑ መሥዋዕትም ለሚሠው ለእንግዶች ሚስቶቹ ሁሉ እንዲሁ አደረገ።
9-10ሁለት ጊዜም ከተገለጠለት፥ ሌሎችንም አማልክት እንዳይከተል ካዘዘው ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ልቡን አርቆአልና፥ እግዚአብሔርም ያዘዘውን ነገር አልጠበቀምና እግዚአብሔር ሰሎሞንን ተቈጣ። 11እግዚአብሔርም ሰሎሞንን አለው “ይህን ሠርተሃልና፥ ያዘዝሁህንም ቃል ኪዳኔንና ሥርዐቴን አልጠበቅህምና መንግሥትህን ከአንተ ቀዳድጄ ለባሪያህ እሰጠዋለሁ። 12ነገር ግን ከልጅህ እጅ እቀድደዋለሁ እንጂ ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ይህን በዘመንህ አላደርግም። 13ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጣለሁ እንጂ መንግሥቱን ሁሉ አልቀድድም።”
በሰሎሞን ላይ የተነሡበት ጠላቶች
14እግዚአብሔርም ከኤዶምያስ ነገሥታት ዘር የኤዶምያስን ሰው ሃዳድን ጠላት አድርጎ በሰሎሞን ላይ አስነሣው። 15-16ኢዮአብና እስራኤልም ሁሉ የኤዶምያስን ወንድ ሁሉ እስኪገድሉ ድረስ ስድስት ወር በዚያ ተቀምጠው ነበርና ዳዊት በኤዶምያስ በነበረ ጊዜ፥ የሠራዊቱም አለቃ ኢዮአብ ተወግተው የሞቱትን ሊቀብር በወጣ ጊዜ፥ የኤዶምያስንም ወንድ ሁሉ በገደለ ጊዜ፥ 17ሃዳድ ገና ብላቴና ሳለ ሃዳድና ከእርሱ ጋር ጥቂቶቹ ከኤዶምያስ ሰዎች የሆኑ የአባቱ ባሪያዎች ወደ ግብጽ ኰብልለው ነበር። 18ከምድያምም ተነሥተው ወደ ፋራን መጡ፤ ከእነርሱም ጋር ከፋራን ሰዎች ወሰዱ፤ ወደ ግብጽም መጡ፤ ወደ ግብጽም ንጉሥ ወደ ፈርዖን ዘንድ ገቡ፤ እርሱም ቤት ሰጥቶ ቀለብ ዳረገው፤ ምድርም ሰጠው። 19የሚስቱንም የእቴጌይቱን የቴቄምናስን እኅት እስኪያጋባው ድረስ ሃዳድ በፈርዖን ፊት እጅግ ባለምዋል ሆነ። 20የቴቄምናስ እኅት ጌንባትን ወለደችለት፤ ቴቄምናስም በፈርዖን ቤት አሳደገችው፤ ጌንባትም በፈርዖን ቤት በፈርዖን ልጆች መካከል ነበረ። 21ሃዳድም በግብጽ ሳለ ዳዊት ከአባቶቹ ጋር እንዳንቀላፋ፥ የሠራዊቱም አለቃ ኢዮአብ እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ፥ ሃዳድ ፈርዖንን “ወደ አገሬ እሄድ ዘንድ አሰናብተኝ፤” አለው። 22ፈርዖንም “እነሆ፥ ከእኔ ዘንድ ወደ አገርህ መሄድ የፈለግህ ምን አጥተህ ነው?” አለው። እርሱም “አንዳች አላጣሁም፤ ነገር ግን ልሂድ፤” ብሎ መለሰ። ሃዳድም ወደ አገሩ ተመለሰ፤ ሃዳድም ያደረገው ክፉ ነገር ይህ ነው፤ እስራኤልን አስጨነቀ፤ በኤዶምያስም ላይ ነገሠ።
23እግዚአብሔርም ደግሞ ከጌታው ከሱባ ንጉሥ ከአድርአዛር የኰበለለውን የኤልያዳን ልጅ ሬዞንን ጠላት አድርጎ አስነሣበት። 24ዳዊትም የሱባን ሰዎች በገደለ ጊዜ ሬዞን ሰዎችን ሰብስቦ የጭፍራ አለቃ ሆነ፤ ወደ ደማስቆም ሄዱ፤ በዚያም ተቀመጡ፤ በደማስቆም ላይ አነገሡት። 25ሃዳድም ካደረገው ክፋት ሌላ በሰሎሞን ዘመን ሁሉ የእስራኤል ጠላት ነበረ።
እግዚአብሔር ለኢዮርብዓም የሰጠው ተስፋ
26ከሳሪራ አገር የሆነ የሰሎሞን ባሪያ የኤፍሬማዊው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በንጉሡ ላይ ዐመፀ፤ እናቱም ጽሩዓ የተባለች ባልቴት ሴት ነበረች። 27በንጉሡም ያመፀበት ምክንያት ይህ ነው፤ ሰሎሞን ሚሎን ሠራ፤ የአባቱንም የዳዊትን ከተማ ሰባራውን ጠገነ። 28ኢዮርብዓምም ጽኑዕ ኀያል ሰው ነበረ፤ ሰሎሞንም ጐልማሳው በሥራ የተመሰገነ መሆኑን ባየ ጊዜ በዮሴፍ ነገድ ሥራ ሁሉ ላይ ሾመው። 29በዚያን ጊዜም ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ሴሎናዊው ነቢዩ አኪያ በመንገድ ላይ ተገናኘው፤ አኪያም አዲስ ልብስ ለብሶ ነበር፤ ሁለቱም በሜዳው ለብቻቸው ነበሩ። 30አኪያም የለበሰውን አዲስ ልብስ ይዞ ከዐሥራ ሁለት ቆራረጠው። 31ኢዮርብዓምንም አለው “ዐሥር ቁራጭ ውሰድ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና ‘እነሆ፥ ከሰሎሞን እጅ መንግሥቱን እቀድዳለሁ፤ ዐሥሩንም ነገዶች እሰጥሃለሁ፤ 32ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ከእስራኤልም ነገድ ስለ መረጥኋት ከተማ ስለ ኢየሩሳሌም ግን አንድ ነገድ ይቀርለታል፤ 33ጥለውኛልና፥ ለሲዶናውያንም አምላክ ለአስታሮት፥ ለሞዓብም አምላክ ለካሞሽ፥ ለአሞንም ልጆች አምላክ ለሚልኮም ሰግደዋልና፥ አባቱም ዳዊት እንዳደረገ በፊቴ ቅን ነገር ያደርጉ ዘንድ፥ ሥርዐቴንና ፍርዴንም ይጠብቁ ዘንድ በመንገዴ አልሄዱምና። 34መንግሥቱንም ሁሉ ከእጁ አልወስድም፤ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ስለ ጠበቀው ስለ መረጥሁት ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ግን በዕድሜው ሁሉ አለቃ አደርገዋለሁ። 35መንግሥቱንም ከልጁ እጅ እወስዳለሁ፤ ለአንተም ዐሥሩን ነገድ እሰጥሃለሁ። 36ስሜንም ባኖርሁባት በዚያች በመረጥኋት ከተማ በኢየሩሳሌም ለባሪያዬ ለዳዊት በፊቴ ሁልጊዜ መብራት ይሆንለት ዘንድ ለልጁ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ። 37አንተንም እወስድሃለሁ፤ ነፍስህም በወደደችው ሁሉ ላይ ትነግሣለች፤ በእስራኤልም ላይ ንጉሥ ትሆናለህ። 38ባሪያዬም ዳዊት እንዳደረገ፥ ያዘዝሁህን ሁሉ ብትሰማ፥ በመንገዴም ብትሄድ፥ በፊቴም የቀናውን ብታደርግ፥ ሥርዐቴንና ትእዛዜን ብትጠብቅ፥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ለዳዊትም እንደ ሠራሁለት ጽኑ ቤት እሠራልሃለሁ፤ እስራኤልንም ለአንተ እሰጥሃለሁ። 39ስለዚህም የዳዊትን ዘር አስጨንቃለሁ፤ ነገር ግን በዘመን ሁሉ አይደለም።’” 40ሰሎሞንም ኢዮርብዓምን ሊገድለው ወደደ፤ ኢዮርብዓምም ተነሥቶ ወደ ግብጽ ኮበለለ፤ ወደ ግብጽም ንጉሥ ወደ ሺሻቅ መጣ፤ ሰሎሞንም እስኪሞት ድረስ በግብጽ ተቀመጠ።
የሰሎሞን መሞት
(2ዜ.መ. 9፥29-31)
41የቀረውም የሰሎሞን ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጥበቡም፥ እነሆ፥ በሰሎሞን ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 42ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም በእስራኤል ሁሉ ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነበረ። 43ሰሎሞንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓም በፋንታው ነገሠ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 11: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ