የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3:10-23

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3:10-23 አማ54

የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፥ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል። ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል፤ የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፥ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ። ማንም ራሱን አያታልል፤ ከእናንተ ማንም በዚች ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን። የዚህች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነውና። እርሱ ጥበበኞችን በተንኵኦላቸው የሚይዝ፤ ደግሞም፦ ጌታ የጥበበኞችን አሳብ ከንቱ እንደ ሆነ ያውቃል ተብሎ ተጽፎአልና። ስለዚህም ማንም በሰው አይመካ። ነገር ሁሉ የእናንተ ነውና፤ ጳውሎስ ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም ቢሆን፥ ሁሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው።