የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 23

23
የሌዋውያን አገልግሎት
1ዳዊትም በሸመገለ ጊዜ፥ ዕድሜንም በጠገበ ጊዜ ሰሎሞንን በእስራኤል ላይ አነገሠው። 2የእስራኤልንም አለቆች ሁሉ፥ ካህናቱንም፥ ሌዋውያኑንም ሰበሰበ። 3ሌዋውያንም ከሠላሳ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ወደ ላይ ተቈጠሩ፤ ቍጥራቸው በእያንዳንዳንዱ ነፍስ ወከፍ ሠላሳ ስምንት ሺህ ነበር። 4ከእነዚህም ውስጥ የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ የሚሠሩት ሃያ አራት ሺህ ነበሩ። ስድስቱ ሺህም አለቆችና ፈራጆች ነበሩ። 5አራቱ ሺህም በረኞች ነበሩ፤ አራቱ ሺህም ለምስጋና በተሰሩት በዜማ ዕቃዎች እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር።
6ዳዊትም እንደ ሌዊ ልጆች እንደ ጌድሶንና እንደ ቀዓት እንደ ሜራሪም በየሰሞናቸው ከፈላቸው።
ጌድሶናውያን
7ከጌድሶናውያን ለአዳንና ሰሜኢ ነበሩ። 8የለአዳን ልጆች አለቃው ይሒኤል፥ ዜቶም፥ ኢዮኤል ሦስት ነበሩ። 9የሰሜኢ ልጆች ሰሎሚት፥ ሐዝኤል፥ ሐራን ሦስት ነበሩ። እነዚህ የለአዳን አባቶች ቤቶች አለቆች ነበሩ። 10የሰሜኢ ልጆች ኢኢት፥ ዚዛ፥ የዑስ፥ በሪዓ ነበሩ። እነዚህ አራቱ የሰሜኢ ልጆች ነበሩ። 11አለቃው ኢኢት ነበረ፤ ሁለተኛው ዚዛ ነበረ፤ የዑስና በሪዓ ግን ብዙ ልጆች አልነበሩአቸውም፤ ስለዚህ እንደ አንድ አባት ቤት ሆነው ተቈጠሩ።
ቀዓታውያን
12የቀነዓት ልጆች እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል አራት ነበሩ። 13የእንበረም ልጆች አሮንና ሙሴ ነበሩ፤ አሮንም ከሁሉ በላይ የተቀደሰ ይሆን ዘንድ ተለየ፤ እርሱና ልጆቹ፥ ለዘላለም በእግዚአብሔር ፊት ያጥኑና ያገለግሉ ዘንድ፥ በስሙም ለዘለአለም ይባርኩ ዘንድ። 14የእግዚአብሔርም ሰው የሙሴ ልጆች በሌዊ ነገድ ተቈጠሩ። 15የሙሴ ልጆች ጌርሳምና አልዓዛር ነበሩ። 16የጌርሳም ልጆች አለቃ ሱባኤል ነበረ። 17የአልዓዛርም ልጆች አለቃ ረዓብያ ነበረ፤ አልዓዛርም ሌሎች ልጆች አልነበሩትም፤ የረዓብያ ልጆች እጅግ ብዙ ነበሩ። 18የይስዓር ልጆች አለቃው ሰሎሚት ነበረ። 19የኬብሮን ልጆች አለቃው ይሪያ፥ ሁለተኛው አማሪያ፥ ሦስተኛው የሕዚኤል፥ አራተኛው ይቅምዓም ነበሩ። 20የዑዝኤል ልጆች አለቃው ሚካ፥ ሁለተኛው ይሺያ ነበሩ።
ሜራሪያውያን
21የሜራሪ ልጆች ሞሖሊና ሙሲ ነበሩ። የሞሖሊ ልጆች አልዓዛርና ቂስ ነበሩ። 22አልአዛርም ሴቶች ልጆች ብቻ እንጂ ወንዶች ልጆች ሳይወልድ ሞተ፤ ወንድሞቻቸውም የቂስ ልጆች አገቡአቸው። 23የሙሲ ልጆች ሞሖሊ፥ ዔደር፥ ኢያሪሙት ሦስት ነበሩ።
24የእግዚአብሔርን ቤት አገልግሎት በሠሩ ከሃያ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ወደ ላይ በነበሩ በእያንዳንዳቸው በስማቸው በተቈጠሩት ላይ የአባቶች ቤት አለቆች የሆኑት በየአባቶቻቸው ቤት የሌዊ ልጆች እነዚህ ነበሩ። 25ዳዊትም “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ዕረፍት ሰጥቶአል፤ በኢየሩሳሌምም ለዘላለም ይቀመጣል። 26ሌዋውያንም ከእንግዲህ ወዲህ ማደሪያውንና የማገልገያውን ዕቃ ሁሉ አይሸከሙም፤” አለ። 27በመጨረሻውም በዳዊት ትእዛዝ ከሃያ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት የሌዊ ልጆች ተቈጠሩ። 28ሥራቸውም የእግዚአብሔርን ቤት በየአደባባዩና በየጓዳው ውስጥ ለማገልገል፥ ቅዱሱንም ዕቃ ሁሉ ለማንጻት፥ የእግዚአብሔርንም ቤት አገልግሎት ለመሥራት ከአሮን ልጆች እጅ በታች ነበረ። 29ደግሞም ገጸ ኅብስት፥ ስስ ቂጣም ቢሆን፥ በምጣድም ቢጋገር፥ ቢለወስም፥ ለእህል ቍርባን በሆነው በመልካሙ ዱቄት በመስፈሪያና በልክ ሁሉ ያገልግሉ ነበር። 30ሥራቸውም በየጥዋቱና በየማታው ቆመው እግዚአብሔርን ለማመስገንና ለማክበር፥ 31በየሰንበታቱም በየመባቻዎቹም በየበዓላቱም እንደ ሥርዐቱ ቍጥር በእግዚአብሔር ፊት ዘወትር ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁሉ ለማቅረብ፥ 32ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት የመገናኛውን ድንኳን ሥርዓት የመቅደሱንም ሥርዓት የወንድሞቻቸውንም የአሮንን ልጆች ሥርዓት ለመጠበቅ ነበረ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ