አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 15
15
የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ለመውሰድ የተደረገ ዝግጅት
1ዳዊትም በከተማው ላይ ለራሱ ቤቶችን ሠራ፤ ለእግዚአብሔርም ታቦት ስፍራ አዘጋጀ፤ ድንኳንም ተከለለት። 2በዚያን ጊዜም ዳዊት “የእግዚአብሔርን ታቦት ይሸከሙ ዘንድ፥ ለዘላለሙም ያገለግሉት ዘንድ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ከሌዋውያን በቀር ማንም የእግዚአብሔርን ታቦት ይሸከም ዘንድ አይገባውም፤” አለ። 3ዳዊትም ወዳዘጋጀለት ስፍራ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጣ ዘንድ እስራኤልን ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 4ዳዊትም የአሮንን ልጆችና ሌዋውያንን ሰበሰበ። 5ከቀዓት ልጆች አለቃው ኡርኤል፥ ወንድሞቹም መቶ ሀያ፤ 6ከሜራሪ ልጆች አለቃው ዓሣያ፥ ወንድሞቹም ሁለት መቶ ሀያ፤ 7ከጌድሶን ልጆች አለቃው ኢዮኤል፥ ወንድሞቹም መቶ ሠላሳ፤ 8ከኤሊጻፋን ልጆች አለቃው ሸማያ፥ ወንድሞቹም ሁለት መቶ፤ 9ከኬብሮን ልጆች አለቃው ኤሊኤል፥ ወንድሞቹም ሰማንያ፤ 10ከዑዝኤል ልጆች አለቃው አሚናዳብ፥ ወንድሞቹም መቶ ዐሥራ ሁለት። 11ዳዊትም ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን፥ ሌዋውያንንም ኡርኤልን፥ ዓሣያን፥ ኢዮኤልን፥ ሸማያን፥ ኤሊኤልን፥ አሚናዳብንም ጠርቶ 12“እናንተ የሌዋውያን አባቶች ቤቶች አለቆች ናችሁ፤ ወዳዘጋጀሁለት ስፍራ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ታመጡ ዘንድ እናንተና ወንድሞቻችሁ ተቀደሱ። 13ቀድሞም አልተሸከማችሁምና፥ እንደ ሥርዐቱም አልፈለግነውምና አምላካችን እግዚአብሔር በመካከላችን ስብራት አደረገ፤” አላቸው። 14የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጡ ዘንድ ካህናቱና ሌዋውያኑ ተቀደሱ። 15ሙሴም እንዳዘዘው እንደ እግዚአብሔር ቃል የሌዋውያን ልጆች የእግዚአብሔርን ታቦት በትከሻቸው ላይ በመሎጊያዎቹ ተሸከሙ።
16ዳዊትም በዜማ ዕቃ በመሰንቆና በበገና በጸናጽልም እንዲያዜሙ፥ ድምፃቸውንም በደስታ ከፍ እንዲያደርጉ መዘምራኑን ወንድሞቻቸውን ይሾሙ ዘንድ ለሌዋውያን አለቆች ተናገረ። 17ሌዋውያኑም የኢዮኤልን ልጅ ኤማንን፥ ከወንድሞቹም የበራክያን ልጅ አሳፍን፥ ከወንድሞቻቸውም ከሜራሪ ልጆች የቂሳን ልጅ ኤታንን፥ 18ከእነርሱም ጋር በሁለተኛው ተራ የሆኑትን ወንድሞቻቸውን ዘካርያስን፥ ቤንን፥ ያዝኤልን፥ ሰሚራሞትን፥ ይሒኤልን፥ ዑኒን፥ ኤልያብን፥ በናያስን፥ መዕሤያን፥ መቲትያን፥ ኤሊፍሌሁን፥ ሚቅኔያን፥ በረኞችንም ዖቤድኤዶምንና ይዒኤልን አቆሙ። 19መዘምራንም ኤማን አሳፍና ኤታን በናስ ጸናጽል ከፍ አድርገው ያሰሙ ነበር። 20ዘካርያስ፥ ዓዝዔል፥ ሰሚራሞት፥ ይሒኤል፥ ዑኒ፥ ኤልያብ፥ መዕሤያና በናያስ በመሰንቆ ምሥጢር ነገር ያዜሙ ነበር። 21መቲትያ፥ ኤልፍሌሁ፥ ሚቅኔያ፥ ዖቤድኤዶም፥ ይዒኤልና ዓዛዝያ ስምንት አውታር ባለው በገና ይዘምሩ ነበር። 22የሌዋውያኑም አለቃ ክናንያ በዜማ ላይ ተሾሞ ነበር። ብልሃተኛ ነበረና ዜማ ያስተምራቸው ነበር። 23በራክያና ሕልቃናም ለታቦቱ በረኞች ነበሩ። 24ካህናቱም ሰበኒያ፥ ኢዮሣፍጥ፥ ናትናኤል፥ ዓማሣይ፥ ዘካርያስ፥ በናያስና አልዓዛር በእግዚአብሔር ታቦት ፊት መለከት ይነፉ ነበር። ዖቤድኤዶምና ይሒያም ለታቦቱ በረኞች ነበሩ።
የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም መወሰዱ
(2ሳሙ. 6፥12-19)
25ዳዊት፥ የእስራኤል ሽማግሌዎችና ሻለቆች የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከአቢዳራ ቤት በደስታ ያመጡ ዘንድ ሄዱ። 26የእግዚአብሔርንም ቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙትን ሌዋውያንን እግዚአብሔር በረዳቸው ጊዜ ሰባት በሬዎችና ሰባት አውራ በጎች ሰዉ። 27ዳዊትም፥ ታቦቱንም የተሸከሙ ሌዋውያን ሁሉ፥ መዘምራኑም፥ የመዘምራኑም አለቃ ከናንያ የጥሩ በፍታ ቀሚስ ለብሰው ነበር፤ ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ ነበረው። 28እንዲሁ እስራኤል ሁሉ “ሆ!” እያሉ፥ ቀንደ መለከትና እምቢልታ እየነፉ፥ ጸናጽል መሰንቆና በገና እየመቱ፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት አመጡ።
29የእግዚአብሔርም ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በደረሰ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሡም ዳዊት ሲዘፍንና ሲጫወት አይታ በልብዋ ናቀችው።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 15: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ