አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 14
14
ከኪራም ወደ ዳዊት የተላኩ ሠራተኞች
(2ሳሙ. 5፥11-12)
1የጢሮስም ንጉሥ ኪራም ቤት ይሠሩለት ዘንድ መልእክተኞችን የዝግባ እንጨትንም ጠራቢዎችንም አናጢዎችንም ወደ ዳዊት ላከ። 2ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል መንግሥቱ ከፍ ብሎአልና እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናው ዳዊት አወቀ።
ዳዊት በኢየሩሳሌም የመሠረተው ቤተሰብ
(3፥5-9፤ 2ሳሙ. 5፥13-16)
3ዳዊትም በኢየሩሳሌም ሚስቶችን ጨምሮ ሌሎችን ወንዶችና ሴቶችን ልጆች ወለደ። 4በኢየሩሳሌምም የወለዳቸው የልጆቹ ስም ይህ ነው፤ ሳሙስ፥ ሶባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥ 5ኢያቤሐር፥ ኤሊሱዔ፥ ኤሊፋላት፥ 6ኖጋ፥ ናፌቅ፥ ያፍያ፥ 7ኤሊሳማ፥ ኤሊዳሄ፥ ኤሊፋላት።
ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል እንዳደረገ
(2ሳሙ. 5፥17-25)
8ፍልስጥኤማያንም ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ ሆኖ እንደተቀባ ሰሙ፤ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ዳዊትን ሊፈልጉ ወጡ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ሊጋጠማቸው ወጣ። 9ፍልስጥኤማውያንም መጥተው በራፋይም ሸለቆ አደጋ ጣሉ። 10ዳዊትም “ወደ ፍልስጥኤማውያን ልውጣን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም “በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና ውጣ፤” አለው። 11ወደ በኣልፐራሲምም ወጡ፤ በዚያም ዳዊት መታቸው። ዳዊትም “ውሃ እንዲያፈርስ እግዚአብሔር ጠላቶቼን በእጄ አፈረሳቸው፤” አለ። ስለዚህም የዚያን ስፍራ ስም “በኣልፐራሲም” ብለው ጠሩት። 12አማልክቶቻቸውንም በዚያ ተዉ፤ ዳዊትም አዘዘ፤ በእሳትም አቃጠሉአቸው።
13ፍልስጥኤማውያንም ደግሞ በሸለቆው አደጋ ጣሉ። 14ዳዊትም እንደ ገና እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም “ከእነርሱ ዞረህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ ወደ እነርሱ አትውጣ። 15በሾላውም ዛፍ ራስ ውስጥ የሽውሽውታ ድምፅ ስትሰማ የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ሊመታ እግዚአብሔር በፊትህ ይወጣልና በዚያን ጊዜ ወደ ሰልፍ ውጣ፤” አለው። 16ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ከገባዖንም ጀምሮ እስከ ጌዝር ድረስ የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መቱት። 17የዳዊትም ዝና በየአገሩ ሁሉ ወጣ፤ መፈራቱንም እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ አደረገው።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 14: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ