መጽሐፈ ሲራክ 8
8
1በእጃቸው እንዳትወድቅ
ከታላላቆች ሰዎች ጋር አትከራከር።
2በብልጽግናው ድል እንዳያደርግህ ከባለጸጋ ጋር አትጣላ፥
ብዙዎች ስለ ወርቅ ጠፍተዋልና፤
የነገሥታትም ልቡና ድል ሆኖአልና።
3ከተናጋሪ ሰውም ጋር አትከራከር፤
ያለዚያ በእሳት ላይ እንጨት መከመርህ ነው።
4እናትና አባትህን እንዳታዋርድ፥
ከአላዋቂ ሰው ጋር አትሣቅ።
5ከኀጢአቱ የተመለሰውን ሰው አትንቀፈው፤
እኛ ሁላችንም ኀጢአተኞች እንደሆን ዐስብ።
6በርጅናው ጊዜ ሰውን አታቅልለው፥
ከእኛ የማያረጅ የለምና።
7በሞተ ሰው ደስ አይበልህ፤
ሁላችንም እንደምንሞት ዐስብ።
8የብልሆችን ነገር አታቃልል፤
ጥበብን በእነርሱ ዘንድ ታገኛለህና፥ ምሳሌያቸውን ተማር።
መምህራንንም አገልግል።
9የሽማግሎችን ምክራቸውን ጠብቅ፤
እነርሱ ከአባቶቻቸው ተምረዋልና
አንተም ከእነርሱ ተማር፤
በኀዘንህም ጊዜ የምትናገረውን ታገኛለህ
የምትመልሰውንም ታውቃለህ።
10በእሳታቸው እንዳትቃጠል፥
የኀጢአተኞች ሰዎችን እሳት አትጫር።
11በአንደበቱ ነገር እንዳያስትህ፥
በተሳዳቢና በጠላት ዘንድ አትከራከር።
12ከአንተ ለሚበለጽገው አታበድረው፤
ብታበድረው ግን ገንዘብህን እንዳጣህ ዕወቅ።
13ከአንተ ለሚበረታውም አቷሰው፤
ብቷሰው ግን አንተ ራስህ እንደምትከፍል ዐስብ።
14ከዳኛ ጋር አትከራከር፥
እንደ ክብሩ መጠን ፍርድን ይለውጡለታልና፤
15እንዳይደፍርህ ከደፋር ሰው ጋራ መንገድን አትሂድ፤
እርሱ ልቡ እንደ ወደደ ያደርጋልና
አንተም በእርሱ ስንፍና ትሞታለህ።
16ከቍጡ ሰው ጋር አትከራከር፤
በእርሱ ዘንድ ደም ማፍሰስ እንደ ኢምንት ነውና፥
ረዳት ወደሌለበት ቦታም ይወስድሃልና
ከእርሱ ጋር ወደ ምድረ በዳ አትውጣ።
17የሰማውን ነገር መጠበቅ አይችልምና፥
ከአላዋቂ ሰው ጋራ አትማከር።
18እንዴት እንደሚደርስብህ አታውቅምና፥
ጉዳይህን በባዕድ ፊት አትናገር።
19ዋጋህ እንዳይጠፋብህ፥
ለሰው ሁሉ የልብህን ምሥጢር አትግለጥ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 8: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ