መጽሐፈ ሲራክ 7
7
1ክፋትን አትሥራት፤
ክፉም አያገኝህም።
2ከበደል ራቅ፥
እርሷም ራስዋ ካንተ ትርቃለች።
3ሰባት እጥፍ አድርገህ እንዳትሰበስባት፥
በኀጢአት ትልም አትዝራ።
4ከእግዚአብሔር መንግሥትን አትለምን፤
ከንጉሥም የክብር ዙፋን አትለምን።
5በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ነኝ አትበል፤
በንጉሥም ዘንድ ብልህ ነኝ አትበል።
6ዳኛ መሆንን አትውደድ፤
እነሆ፥ በደለኛውን ለመበቀል አትችልም ይሆናል፤
እነሆ፥ ለባለጸጋም ታደላ ይሆናል፤
በእውነት ሥራህም ላይ ኀጢአት ትሠራለህ።
7ያገርህንም ሰው አትበድል፤
ራስህንም በወገኖችህ መካከል አታስት።
8በአንዲቱም ቢሆን ከቅጣት አታመልጥምና፥
ሁለት ኀጢአት አንድ አድርገህ አትሥራ።
9በመባዬ ብዛት እግዚአብሔር ኀጢአቴን ያስተሰርይልኛል፤
ለልዑል እግዚአብሔርም መባእ ከአገባሁ ይቅር ይለኛል አትበል።
10በምትጸልይበት ጊዜ አትቸኩል፥
ምጽዋት መመጽወትንም አታቃልል።
11የሚያሳዝን፥ ደስ የሚያሰኝም አለና፥
ባዘነ ሰው አትሳቅ።
12በባልንጀራህ ሐሰትን ተግባር አታድርግ፤
በወዳጅህና በባልንጀራህም ላይ እንዲህ አታድርግ።
13በምንም ሁልጊዜ ሐሰትን አትውደድ፥
ፍጻሜዋ ይጎዳሃልና።
14በሽማግሌዎች መካከል ብዙ ቃል አትናገር፤
በአፍህ የተናገርኸውን ስእለትህን አትመልስ፥ ቃልህንም አትለውጥ።
15የእጅህንም ሥራ አታቃልል፥
ፈጣሪህም የሚያበቅልልህን ቡቃያህን ቸል አትበል።
16ብዙ ናቸው ብለህ
ከኀጢአተኞች ጋር አንድ አትሁን።
17ጥፋት እንደማትዘገይ ዐስብ፥
ሰውነትህን ፈጽመህ አዋርዳት፥
የኀጢአተኞች ፍዳቸው ትልና እሳት ነውና።
18በእየነጋው ወዳጅ አትለውጥ፤
ስለ ቀይ ወርቅ ወዳጅህን አትጣ።
19መወደዷ ከወርቅ ይወደዳልና
ብልህና ደግ ሴትን አትጥላ።
20በእውነት በሚገዛልህ ቤተ ሰብህ ላይ፥
ስለ አንተ ሰውነቱን አሳልፎ በሚሰጥ በምንደኛህም ላይ ክፉ ነገርን አታድርግ።
21ብልህ ቤተ ሰብህን እንደ ራስህ ውደደው፤
ነጻ ታወጣውም ዘንድ ተስፋ ያደረገህን ዋጋውን አታጥፋበት።
22ሁልጊዜ ከብትህን መፍቀድ አትተው፤
ከእነርሱ የሚጠቅምህን ወደ አንተ አቅርብ።
23ልጆች ቢኖሩህ ምከራቸው፤
ከሕፃንነታቸው ጀምረህ ትሕትናን አስተምራቸው።
24ሴቶች ልጆችም ቢኖሩህ ጠብቃቸው፤
አታስታቸው፥ አትሣቅላቸው፥ አታባብላቸውም።
25ልጅህን አቅመ ሔዋን ስታደርስ አጋባት፥
ጠብቃት፥ ታላቅ ሥራንም ትፈጽማለህ፥ ከድካምም ታርፋለህ፥
ነገር ግን ለብልህ ሰው አጋባት።
26እንደ ራስህ የምትወዳት ሚስት ብትኖርህ አትፍታት።
27በፍጹም ልቡናህ አባትህን አክብረው፥
የእናትህንም ምጧን አትዘንጋ።
28በእነርሱም ምክንያት እንደ ተወለድህ ዐስብ፤
ስላደረጉልህስ ፋንታ ምን ታደርግላቸዋለህ?
29በፍጹም ሰውነትህ እግዚአብሔርን ፍራው፤
ካህናቱንም አክብራቸው።
30በፍጹም ኀይልህም ፈጣሪህን ውደደው፤
የሚያገለግሉትንም አትተዋቸው።
31እግዚአብሔርን ፍራው፤
የሚያገለግለውን ካህኑንም አክብረው፤
የታዘዘልህ ዕድሉንም ስጠው፤
ቀዳምያቱንና፥ ስለ ኀጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት፥
ወርቹንም፥ ማታና ጧትም የሚሠዋውን መሥዋዕት፥
መጀመሪያ የሚወለደውንም ከብት ስጠው።
32በረከትህ ፍጽምት ትሆን ዘንድ
እጅህን ለድሃ ዘርጋ።
33ስጦታ በሕያው ሁሉ ፊት ጸጋ አለው፥
ስለ ሞተ ሰውም ምጽዋት መስጠትን አትተው።
34ከሚያለቅሱ ሰዎችም አትለይ፥
ከሚያለቅሱም ጋር አልቅስ።
35ሕመምተኛንም ሰው መጐብኘት ቸል አትበል፥
በዚህም ይወዱሃል።
36በተናገርኸው ነገር ሁሉ ፍጻሜህን ዐስባት፥
ሁልጊዜም አትበድል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 7: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ