መጽሐፈ ሲራክ 3
3
ልጆች ለወላጆቻቸው ማድረግ ያለባቸው ግዴታ
1ልጆች ሆይ፥ እኔን አባታችሁን ስሙኝ፥
በሕይወት ትኖሩ ዘንድ እንዲህ አድርጉ፤
2እግዚአብሔር አባትን በልጆች ላይ አክብሯልና።
የእናትንም ሥልጣን በልጆችዋ ላይ ከፍ ከፍ አድርጎአልና።
3አባቱን የሚያከብር ልጅ ኀጢአቱ ይሰረይለታል።
4እናቱንም የሚያከብራት ልጅ ድልብ እንደሚያደልብ ነው።
5አባቱን የሚያከብር ልጅ በልጆቹ ደስ ይለዋል፤
በሚጸልይበትም ቀን ፈጣሪው ይሰማዋል።
6አባቱን የሚያከብር ልጅ ዕድሜው ይረዝምለታል።
7እግዚአብሔርን የሚሰማ ልጅ እናቱን ያሳርፋታል።
8እንደ አገልጋዮቹም ለወላጁ ይገዛል።
9በረከቱ ትደርስህ ዘንድ
በቃልህም በሥራህም አባትህን አክብረው።
10የአባት በረከት የልጅን ቤት ያጸናልና፥
የእናት ርግማን ግን መሠረትን ይነቅላል።
11አባትህን በማቃለል አትመካ፤
አባትህን ማቃለል ትምክሕት አይሆንህምና
ሰው በአባቱ ክብር ይከብራል፤
የሰውም ውርደቱ እናቱን በማቃለሉ ነው።
12ልጄ ሆይ፥ በእርጅናው ጊዜ አባትህን ርዳው፥
በሕይወቱም ሳለ አታሳዝነው።
13ቢያረጅ፥ አእምሮውንም ቢያጣ ለፈቃዱ እሺ በለው፥
እንደሚቻልህም አክብረው፥ በአረጀም ጊዜ አታስከፋው፥
ዋጋ በመቀበል ጊዜ አባትህን መርዳትህ አይዘነጋብህምና።
14ስለ ኀጢአትም ፋንታ ጽድቅ ትሠራልሃለች።
15በመከራህም ቀን ይታሰብልሃል፤
ፀሐይ በረድን እንደሚያቀልጠው ኀጢአቶችህ እንደዚሁ ይቀልጣሉ።
16አባቱን የሚጥል ሰው እግዚአብሔርን እንደሚፀርፍ ነው፤
እናቱን የሚያሳዝናትም በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነው።
ስለ ትሕትና
17ልጄ ሆይ፥ ሥራህ በሃይማኖትህ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በየዋህነት” ይላል። ይገለጥ፤
እውነተኞች ሰዎችም ይወድዱሃል።
18እንደ ገናንነትህ መጠን እንደዚሁ ራስህን አዋርድ።
በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋህን ታገኛለህ።
19የእግዚአብሔር ሥራው ታላቅ ነውና፥
በቅዱሳንና#“ቅዱሳን” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። በትሑታን ዘንድ ይመሰገናል።
20የሚበረታብህን አትፈልግ፤
የማትችለውንም አትመርምር፤
21ነገር ግን የታዘዝኸውን ዐስብ።
በስውር ያለው ግን አያስጨንቅህ።
22አላስፈላጊ ሥራዎችን አትመራመር፤
ከሰዎች ይልቅ ለአንተ እጅግ ተገልጦልሃልና።
23ብዙ ሰዎችን መታበያቸው አሳታቸው።
ብዙ ሰዎችንም የልቡናቸው ትዕቢት ጣላቸው።
24ጥፋትን የሚወዳት በእርሷ ይሞታል፥
ክፉ ልቡናም በመጨረሻው ይታመማል።
25ክፉ ልቡና በመከራ ይገረፋል፤
ኀጢአተኛ ሰውም በኀጢአቱ ላይ ኀጢአትን ይጨምራል።
26ለትዕቢተኞች ጥፋት ፈውስ የላትም፤
ክፉ ተክል በውስጣቸው ሥር ሰድዶአልና።
27የብልህ ሰው ልቡና ምሳሌን ይተረጕማል፤
የዐዋቂ ሰው ጆሮም ጥበብ መስማትን ትወዳለች።
ስለ ምጽዋት
28የምትነድድ እሳትን ውኃ ያጠፋታል።
ምጽዋትም ኀጢአትን ታስተሰርያለች።
29ምጽዋትን ለሚሰጥ ሰው በመጨረሻ ይታሰብለታል፤
በሚሰነካከልበትም ጊዜ መጠጊያን ያገኛል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 3: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ