የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮ​ሐ​ንስ ራእይ 5

5
የተዘጋው መጽሐፍና በጉ
1በዙፋኑ ላይም በተቀመጠው በቀኝ እጁ ላይ በውስጥና በኋላ የተጻፈበት በሰባትም ማኅተም የተዘጋ መጽሐፍን አየሁ። 2ብርቱም መልአክ “መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ማኅተሞቹንም ይፈታ ዘንድ የሚገባው ማን ነው?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ሲያውጅ አየሁ። 3በሰማይም ቢሆን በምድርም ላይ ቢሆን ከምድርም በታች ቢሆን መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው ማንም አልተቻለውም። 4መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው የሚገባው ማንም ስላልተገኘ እጅግ አለቀስሁ። 5ከሽማግሌዎቹም አንዱ “አታልቅስ፤ እነሆ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፥ እርሱም የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ሰባቱንም ማኅተም ይፈታ ዘንድ ድል ነሥቶአል፤” አለኝ።
6በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፤ ሰባትም ቀንዶችና ሰባት ዐይኖች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው። 7መጥቶም በዙፋን ላይ ከተቀመጠ ከዚያ ከቀኝ እጁ መጽሐፉን ወሰደው። 8መጽሐፉንም በወሰደ ጊዜ አራቱ እንስሶችና ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ፤ እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ።
9-10“መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል
ታርደሃልና፤ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ
ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ፥
ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፤
በምድርም ላይ ይነግሣሉ፤”
እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ። 11አየሁም፤ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቍጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር፤ 12በታላቅም ድምፅ
“የታረደው በግ ኀይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም
ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል”
አሉ። 13በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ
“በረከትና ክብር ምስጋናም ኀይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም
በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን፤”
ሲሉ ሰማሁ። 14አራቱም እንስሶች ‘አሜን’ አሉ፤ ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ