ለሰባቱም መላእክት “ሄዳችሁ የእግዚአብሔርን ቁጣ ጽዋዎች በምድር ውስጥ አፍስሱ፤” የሚል ታላቅ ድምፅ ከመቅደሱ ሰማሁ። ፊተኛውም ሄዶ ጽዋውን በምድር ውስጥ አፈሰሰ፤ የአውሬውም ምልክት ባለባቸው ለምስሉም በሚሰግዱ ሰዎች ክፉኛ የሚነዘንዝ ቍስል ሆነባቸው። ሁለተኛውም ጽዋውን በባሕር ውስጥ አፈሰሰ፤ እንደ ሞተም ሰው ደም ሆነ፤ በባሕርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ። ሦስተኛውም ጽዋውን በወንዞችና በውሃ ምንጮች ውስጥ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ። የውሃውም መልአክ “ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ! ቅዱስ ሆይ! እንዲህ ስለፈረድህ ጻድቅ ነህ፤ የቅዱሳንንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደምን ደግሞ አጠጥተሃቸዋል፤ የሚገባቸው ነውና፤” ብሎ ሲናገር ሰማሁ። ከመሰዊያውም “አዎን፤ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ! ፍርዶችህ እውነትና ጽድቅ ናቸው፤” ብሎ ሲናገር ሰማሁ። አራተኛውም ጽዋውን በፀሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ሰዎችንም በእሳት ልታቃጥል ተሰጣት። ሰዎችም በታላቅ ትኵሳት ተቃጠሉ፤ በነዚህም መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፤ ክብርንም እንዲሰጡት ንስሓ አልገቡም። አምስተኛውም ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ መንግሥቱም ጨለማ ሆነች፤ ከስቃይም የተነሣ መላሶቻቸውን ያኝኩ ነበር፤ ከስቃያቸውና ከቍስላቸውም የተነሣ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ፤ ከሥራቸውም ንስሓ አልገቡም። ስድስተኛውም ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲሰናዳላቸው ውሃው ደረቀ። ከዘንዶውም አፍና ከአውሬው አፍ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጕንቸሮች የሚመስሉ ሦስት ርኵሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ፤ ምልክት እያደረጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፥ በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደሚሆነው ጦር እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ። “እነሆ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ ኀፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።” በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ እስከተቱአቸው። ሰባተኛውም ጽዋውን በአየር ውስጥ አፈሰሰ፤ ከመቅደሱም ውስጥ “ተፈጽሞአል!” የሚል ታላቅ ድምጽ ከዙፋኑ ወጣ።
የዮሐንስ ራእይ 16 ያንብቡ
ያዳምጡ የዮሐንስ ራእይ 16
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ራእይ 16:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች