የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮ​ሐ​ንስ ራእይ 16

16
ሰባቱ የእግዚአብሔር ቍጣዎች
1ለሰባቱም መላእክት “ሄዳችሁ የእግዚአብሔርን ቁጣ ጽዋዎች በምድር ውስጥ አፍስሱ፤” የሚል ታላቅ ድምፅ ከመቅደሱ ሰማሁ።
2ፊተኛውም ሄዶ ጽዋውን በምድር ውስጥ አፈሰሰ፤ የአውሬውም ምልክት ባለባቸው ለምስሉም በሚሰግዱ ሰዎች ክፉኛ የሚነዘንዝ ቍስል ሆነባቸው።
3ሁለተኛውም ጽዋውን በባሕር ውስጥ አፈሰሰ፤ እንደ ሞተም ሰው ደም ሆነ፤ በባሕርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ።
4ሦስተኛውም ጽዋውን በወንዞችና በውሃ ምንጮች ውስጥ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ። 5የውሃውም መልአክ “ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ! ቅዱስ ሆይ! እንዲህ ስለፈረድህ ጻድቅ ነህ፤ 6የቅዱሳንንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደምን ደግሞ አጠጥተሃቸዋል፤ የሚገባቸው ነውና፤” ብሎ ሲናገር ሰማሁ። 7ከመሰዊያውም “አዎን፤ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ! ፍርዶችህ እውነትና ጽድቅ ናቸው፤” ብሎ ሲናገር ሰማሁ።
8አራተኛውም ጽዋውን በፀሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ሰዎችንም በእሳት ልታቃጥል ተሰጣት። 9ሰዎችም በታላቅ ትኵሳት ተቃጠሉ፤ በነዚህም መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፤ ክብርንም እንዲሰጡት ንስሓ አልገቡም።
10አምስተኛውም ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ መንግሥቱም ጨለማ ሆነች፤ ከስቃይም የተነሣ መላሶቻቸውን ያኝኩ ነበር፤ 11ከስቃያቸውና ከቍስላቸውም የተነሣ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ፤ ከሥራቸውም ንስሓ አልገቡም።
12ስድስተኛውም ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲሰናዳላቸው ውሃው ደረቀ። 13ከዘንዶውም አፍና ከአውሬው አፍ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጕንቸሮች የሚመስሉ ሦስት ርኵሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ፤ 14ምልክት እያደረጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፥ በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደሚሆነው ጦር እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ። 15“እነሆ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ ኀፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።” 16በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ እስከተቱአቸው።
17ሰባተኛውም ጽዋውን በአየር ውስጥ አፈሰሰ፤ ከመቅደሱም ውስጥ “ተፈጽሞአል!” የሚል ታላቅ ድምጽ ከዙፋኑ ወጣ።
18መብረቅና ድምጽም ነጎድጓድም ሆኑ፤ ትልቅም የምድር መናወጥ ሆነ፤ ሰው በምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ መናውጥ ከቶ አልነበረም፤ ከሁሉ በለጠ። 19ታላቂቱም ከተማ በሦስት ተከፋፈለች፤ የአሕዛብም ከተማዎች ወደቁ። ታላቂቱም ባቢሎን የብርቱ ቍጣው ወይን ጠጅ የሞላበትን ጽዋ እንዲሰጣት በእግዚአብሔር ፊት ታሰበች። 20ደሴቶችም ሁሉ ሸሹ፤ ተራራዎችም አልተገኙም። 21በሚዛንም አንድ ታላንት #አንድ ታላንት አርባ ኪሎ ግራም የሚያህል ነው። የሚያህል ታላቅ በረዶ በሰዎች ላይ ከሰማይ ወረደባቸው፤ ሰዎቹም ከበረዶው መቅሰፍት የተነሣ እግዚአብሔርን ተሳደቡ፤ መቅሰፍቱ እጅግ ታላቅ ነውና።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ