ልጄ ሆይ፥ ለወዳጅህ ዋስ ብትሆን፥ እጅህን ለባላጋራህ ትሰጣለህ፤ የሰው ከንፈሩ ጽኑ ወጥመድ ነው፤ በአፉ ቃል ይጠፋል። ልጄ ሆይ፥ እኔ የማዝዝህን አድርግ፤ ራስህንም አድን፤ ስለ ወዳጅህ በክፉዎች እጅ ወድቀሃልና፤ ሰነፍ አትሁን፥ የተዋስኸውን ወዳጅህን አነሣሣው። ለዐይንህ እንቅልፍን፥ ለሽፋሽፍቶችህም ሸለብታን አትስጥ፤ እንደ ሚዳቋ ከወጥመድ፥ እንደ ወፍም ከጭራ ወጥመድ ትድን ዘንድ። አንተ ታካች፥ ወደ ገብረ ጕንዳን ሂድ፥ መንገዱንም ተመልክተህ ቅና። ከእርሱም ይልቅ ብልህ ሁን። ጌታ ሳይኖረው፥ መሰማርያ ሳይኖረው፥ የሚያሠራውም ሳይኖረው፥ መብሉን በበጋ ይሰበስባል፥ በመከርም ጊዜ በሰፊ ቦታ ያስቀምጣል። ወይም ወደ ንብ ሂድ፥ ሠራተኛ እንደ ሆነች፥ መልካም ሥራንም እንደምትሠራ ዕወቅ፥ የደከመችበትንም ነገሥታትና ሌሎች ሰዎች ለጤንነት ይወስዱታል። በሁሉም ዘንድ የተወደደች ናት፥ የከበረችም ናት። በአካሏ ደካማ ናት፥ በሥራዋ ግን የጸናች ናት፥ ጥበብን አክብራ አሳየች። አንተ ታካች እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ? ጥቂት ትተኛለህ፥ ጥቂትም ትቀመጣለህ፥ ጥቂት ታሸልባለህ፥ ጥቂትም እጆችህን በደረትህ ታጥፋለህ፤ እንግዲህ ድህነት እንደ ክፉ መልእክተኛ፥ ችግርም እንደ ደኅና ርዋጭ ይመጣብሃል። ሰነፍ ባትሆን ግን ባለጸግነትህ እንደምንጭ ይመጣልሃል፤ ችግርም እንደ ክፉ ርዋጭ ከአንተ ይርቃል።
መጽሐፈ ምሳሌ 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ምሳሌ 6:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች