ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2
2
ከትዕቢት ስለ መራቅ
1አሁንም በክርስቶስ ደስታ፥ ወይም በፍቅር የልብ መጽናናት፥ ወይም የመንፈስ አንድነት፥ ወይም ማዘንና መራራትም በእናንተ ዘንድ ካለ፦ 2እርሱን ብቻ ታስቡ ዘንድ፥ አንድ ልብና አንድ ምክርም ሆናችሁ፥ በፍቅር ትኖሩ ዘንድ ደስታዬን ፈጽሙልኝ። 3በክርክርና ከንቱ ውዳሴን በመውደድ አትሥሩ፤ ትሕትናን በያዘ ልቡና ከራሳችሁ ይልቅ ባልንጀራችሁን አክብሩ እንጂ አትታበዩ። 4ለባልንጀራችሁም እንጂ ለየራሳችሁ ብቻ አታስቡ። 5ፍጹማን የሆናችሁ ሁላችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ እንደ አደረገልን ይህን አስቡ።#ግሪኩ “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይኑር” ይላል። 6ይኸውም የእግዚአብሔር መልኩ ነው፤ ቀምቶ እግዚአብሔር የሆነ አይደለም። 7ነገር ግን የባርያን መልክ ይዞ፥ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ። 8እንደ ሰውም ሆኖ ራሱን አዋረደ፤ ለሞት እስከ መድረስም ታዘዘ፤ ሞቱም በመስቀል የሆነው ነው። 9ስለዚህም እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስምንም ሰጠው። 10ይህም በሰማይና በምድር በቀላያትና#“ቀላያት” የሚለው በግሪኩ የለም። ከምድር በታች ያለ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይሰግድ ዘንድ ነው። 11#ኢሳ. 45፥23። አንደበትም ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር አብ ክብር ጌታ እንደ ሆነ ያምን ዘንድ ነው።
12አሁንም ወንድሞች ሆይ፥ ዘወትር እንደምትሰሙኝ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን፥ ሳልኖርም በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ ሆናችሁ ለድኅነታችሁ ሥሩ። 13ለሚወደው ሥራ የሚረዳችሁ እርሱ እግዚአብሔር ይቅርታውን ይፈጽምላችሁ።#ግሪኩ “ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም፥ ማድረግንም በእናንተ የሚ ሠራ እግዚአብሔር ነውና” ይላል። 14የምትሠሩትን ሁሉ ያለ ማንጐራጐርና ያለ መጠራጠር በፍቅርና በስምምነት ሥሩ።#“በፍቅርና በስምምነት ሥሩ” የሚለው በግሪኩ የለም። 15#ዘዳ. 32፥5። እንደ እግዚአብሔር ልጆች ንጹሓንና የዋሃን ትሆኑ ዘንድ፥ በማያምኑና በጠማሞች ልጆች መካከል ነውር ሳይኖርባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፤ 16የሕይወትን ቃል እያስተማራችሁ፤ ክርስቶስ በሚመጣበት ቀን እኔ እንድመካ፤ የሮጥሁ በከንቱ አይደለምና፤ የደከምሁም በከንቱ አይደለምና። 17ስለ ሃይማኖታችሁም የአምልኮ መሥዋዕትን እሠዋለሁ።#ግሪኩ “በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ተጨምሬ ሕይወቴ እንኳን ቢፈስስ ደስ ይለኛል” ይላል። እነሆም እኔ በእናንተ ደስ ይለኛል፤ 18እናንተም በእኔ ደስ ይበላችሁ። ከእኔም ጋር ሐሤት አድርጉ።
ስለ ጢሞቴዎስና አፍሮዲጡ መላክ
19ጢሞቴዎስን እንድልክላችሁ፥ እኔም ዜናችሁን ሰምቼ ደስ እንዲለኝ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋ አደርጋለሁ። 20ከእርሱ በቀር፥ እንደ እኔ ሆኖ በማስተዋል ግዳጃችሁን የሚፈጽም የለኝምና። 21የክርስቶስን ያይደለ፥ ሁሉም የራሱን ጉዳይ ያስባልና። 22ልጅ አባቱን እንደሚያገለግል፥ በወንጌል ትምህርት እንደ አገለገለኝ፥ የዚህን ሰው ጠባዩን ታውቃላችሁ። 23እንግዲህ እንዴት እንደ አለሁ በዐወቅሁ ጊዜ፥ እርሱን በቶሎ እንደምልከው ተስፋ አደርጋለሁ፤ 24እኔም ፈጥኜ እንደምመጣ በጌታችን አምናለሁ።
25አሁንም አብሮኝ የሚሠራውን ወንድማችንን አፍሮዲጡን ወደ እናንተ ልልከው አስቤአለሁ፤ እርሱም የክርስቶስ ሎሌ ነው፤ ለእናንተም መምህራችሁ ነው፤ ለእኔም ለችግሬ ጊዜ መልእክተኛዬ ነው። 26እንደ ታመመ፥ ለሞትም እንደ ደረሰ መስማታችሁን ዐውቆ ሊያያችሁ ይሻልና።#ግሪኩ “ሁላችሁን ሊያያችሁ ይናፍቃልና እንደ ታመመም ስለ ሰማችሁ ይተክዛል” ይላል። 27ነገር ግን እግዚአብሔር ማረው፤ በኀዘን ላይ ኀዘን እንዳይጨመርብኝ ለእኔም እንጂ ለእሱ ብቻ አይደለም። 28እንድታዩትና ደስ እንዲላችሁ፥ እኔም እንዳላዝን በቶሎ እልከዋለሁ። 29እንግዲህ በጌታችን በፍጹም ደስታ ተቀበሉት፤ እንደዚህ ያሉትንም ሁሉ አክብሩአቸው። 30የእግዚአብሔርን ሥራ ስለ መሥራት እስከ ሞት ደርሶአልና፥ ከእኔ መልእክትም እናንተ ያጐደላችሁትን ይፈጽም ዘንድ ሰውነቱን አሳልፎ ሰጥቶአልና።
Currently Selected:
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ