እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “መብራቶቹን ስታበራ ሰባቱ መብራቶች በመቅረዙ ፊት ያበራሉ ብለህ ለአሮን ንገረው።” አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ በመቅረዙ ፊት መብራቶቹን አበራ። የመቅረዝዋም ሥራዋ እንዲህ ነበረ። ሁለንተናቸው ወርቅ የሆነ አፅቆችዋ ሥረ-ወጥ ነበሩ፤ አበቦችዋም ሁለንተናቸው ሥረ-ወጥ ነበሩ። እግዚአብሔር ሙሴን እንዳሳየው ምሳሌ መቅረዝዋን እንዲሁ አደረገ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ከእስራኤል ልጆች መካከል ሌዋውያንን ወስደህ አንጻቸው። ታነጻቸው ዘንድ እንዲህ ታደርግላቸዋለህ፤ በማንጻት ውኃ ትረጫቸዋለህ፤ ሰውነታቸውን ሁሉ ይላጩ፤ ልብሳቸውንም ይጠቡ፤ ንጹሓንም ይሆናሉ። ከላሞች አንድ ወይፈን፥ ለእህሉም ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄትን ይውሰዱ፤ ሌላውንም የአንድ ዓመት ወይፈን ለኀጢአት መሥዋዕት ይውሰዱ። ሌዋውያንንም በምስክሩ ድንኳን ፊት አቅርብ፤ የእስራኤልንም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሰብስብ። ሌዋውያንንም በእግዚአብሔር ፊት አቅርባቸው፤ የእስራኤልም ልጆች በሌዋውያን ላይ እጃቸውን ይጫኑባቸው። አሮንም ሌዋውያን እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ከእስራኤል ልጆች መካከል ስጦታ አድርጎ፥ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ፊት ይለያቸዋል። ሌዋውያኑም በወይፈኖቹ ራሶች ላይ እጆቻቸውን ይጫኑ፤ ለሌዋውያንም ስለ ማስተስረያ አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፥ ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርብ። ሌዋውያንንም በአሮንና በልጆቹ ፊት አቁማቸው፤ በእግዚአብሔርም ፊት ስጦታ አድርገህ አቅርባቸው። እንዲሁ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይ፤ እነርሱም ለእኔ ይሁኑ።
ኦሪት ዘኍልቍ 8 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘኍልቍ 8:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች