ኦሪት ዘኍልቍ 5
5
ንጹሓን ስላልሆኑ ሰዎች
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“የእስራኤል ልጆች ለምጻሙን ሁሉ ፈሳሽ ነገርም ያለበትን ሁሉ በሰውነቱ#ዕብ. “በሬሳም” ይላል። የረከሰውን ሁሉ ከሰፈሩ እንዲያወጡ እዘዛቸው፤ 3እኔ በመካከሉ የማድርበትን ሰፈራቸውን እንዳያረክሱ ከወንድ እስከ ሴት ከሰፈሩ አውጡአቸው።” 4የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ ከሰፈሩ አወጡአቸው፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው፥ የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ።
ስለ በደል ካሣ
5እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 6“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ወንድ ወይም ሴት ቸል ብለው ወይም ባለማወቅ ሰው ከሚሠራው ኀጢአት ሁሉ የሠሩት ቢኖር፥ 7ያች ሰውነት ብትናዘዝ፥ ያደረገችውንም ኀጢአት ሁሉ ብትናገር የወሰደውን ዓይነቱን ሁሉ ይመልስ። አምስተኛ እጅም ለባለ ገንዘቡ ይጨምር። 8ነገር ግን ይመልስለት ዘንድ ሰውዬው ዘመድ ባይኖረው፥ ስለ በደል ለእግዚአብሔር የሚመልሰው ነገር ለካህኑ ይሁን፤ ይህም ስለ እርሱ ማስተስረያ ከሚደረግበት አውራ በግ ላይ ይጨመር። 9የእስራኤልም ልጆች ለእግዚአብሔር ከሚያቀርቡአቸው የተቀደሱ ነገሮች ሁሉ የመጀመሪያው ለካህኑ ነው። 10የተቀደሰ የሰው ነገር ሁሉ፥ ሰውም ለካህኑ የሚሰጠው ሁሉ ለእርሱ ይሁን።”
ባልዋ ስለሚጠራጠራት ሴት
11እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 12“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ የማንኛውም ሰው ሚስት ከእርሱ ፈቀቅ ብትል፥ በእርሱም ላይ ብትበድል፥ 13ሌላም ሰው ከእርስዋ ጋር ቢተኛ፥ ብታመነዝር፥ ከባልዋም ዐይን ቢሸሸግ፥ እርስዋም ተሰውራ ብትረክስ፥ 14ምስክርም ባይኖርባት፥ በምንዝርም ባትያዝ፥ በባልዋም ላይ የቅንዐት መንፈስ ቢመጣበት፥ እርስዋም ስትረክስ ስለ ሚስቱ ቢቀና ወይም እርስዋ ሳትረክስ የቅንዐቱ መንፈስ ቢመጣበት፥ ስለ ሚስቱም ቢቀና፥ 15ያ ሰው ሚስቱን ወደ ካህኑ ያምጣት፤ የኢፍ መስፈሪያም ዐሥረኛ እጅ ገብስ ዱቄት ቍርባን ስለ እርስዋ ያምጣ፤ የቅንዐት ቍርባን ነውና፥ ኀጢአትንም የሚያሳስብ የመታሰቢያ ቍርባን ነውና ዘይት አያፍስስበት፤ ዕጣንም አይጨምርበት።
16“ካህኑም ያቀርባታል፤ በእግዚአብሔርም ፊት ያቆማታል፤ 17ካህኑም የተቀደሰ ውኃ በሸክላ ማሰሮ ይወስዳል፤ ካህኑም በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ካለው ትቢያ ወስዶ በውኃ ላይ ይረጨዋል፤ 18ካህኑም ሴቲቱን በእግዚአብሔር ፊት ያቆማታል፤ የሴቲቱንም ራስ ይገልጣል፤ በእጅዋም ለመታሰቢያ የሚሆነውን የእህል ቍርባን፥ የቅንዐት ቍርባን ያኖራል፤ በካህኑም እጅ ርግማንን የሚያመጣው መራራ ውኃ ይሆናል። 19ካህኑም ያምላታል፤ ሴቲቱንም እንዲህ ይላታል፦ ሌላ ወንድ አልተኛሽ፥ ባልሽንም አልተውሽ፥ ራስሽንም አላረከስሽ እንደ ሆነ፥ ርግማንን ከሚያመጣ ከዚህ መራራ ውኃ ንጹሕ ሁኚ፤ 20ነገር ግን ባልሽን ትተሽ ረክሰሽ እንደ ሆነ፥ ከባልሽም ሌላ ወንድ ከአንቺ ጋር ተኝቶ እንደ ሆነ፤ 21ካህኑም ሴቲቱን በመርገም መሐላ ያምላታል፤ ካህኑም ሴቲቱን እንዲህ ይበላት፦ እግዚአብሔር የተረገምሽ ያድርግሽ ጎንሽን ያረግፈው ዘንድ እግዚአብሔር ከሕዝብሽ መካከል ለይቶ ያጥፋሽ፤ ሆድሽን ይሰንጥቀው፤ 22ርግማንንም የሚያመጣ ይህ ውኃ ወደ ሆድሽ ይግባ፥ ማኅፀንሽንም ይሰንጥቀው፤ ጎንሽም ይርገፍ። ሴቲቱም፦ ይሁን ይሁን ትላለች።
23“ካህኑም እነዚህን መርገሞች በሰሌዳ ላይ ይጽፋቸዋል፤ በመርገሙም መራራ ውኃ ይደመስሳቸዋል፤ 24የመርገሙን መራራ ውኃ ለሴቲቱ ያጠጣታል፤ የርግማኑም ውኃ ወደ ሆድዋ ይገባል። 25ካህኑም የቅንዐቱን መሥዋዕት ከሴቲቱ እጅ ይወስዳል፤ ያንም መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል፥ ወደ መሠዊያውም ያመጣዋል፤ 26ካህኑም ከእህሉ ቍርባን አንድ እፍኝ ሙሉ ለመታሰቢያው ወስዶ በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል። ከዚያም በኋላ ለሴቲቱ ያን ውኃ ያጠጣታል። 27ውኃውን ካጠጣት በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ ራስዋን አርክሳና ባልዋን ቸል ብላው ከሆነ፤ የመርገሙ መራራ ውኃ ወደ ሆድዋ ይገባል፤#ዕብ. “ገብቶ መራራ ይሆንባታል” ይላል። ሆድዋንም ይሰነጥቀዋል፤ ጎኗም ይረግፋል፤ ሴቲቱም በሕዝብዋ መካከል ለመርገም ትሆናለች። 28ራስዋን ያላረከሰች እንደ ሆነች፥ ያለ ነውርም እንደ ሆነች፥ ያነጻታል፤ ልጆችንም ትወልዳለች።
29“በባልዋ ላይ ለበደለችና ራስዋን ላረከሰች ሴት የቅንዐት ሕግ ይህ ነው፤ 30በሰው ላይ የቅንዐት መንፈስ ቢመጣ፥ ስለ ሚስቱም ቢቀና፤ ሴቲቱን በእግዚአብሔር ፊት ያቆማታል፤ 31ካህኑም ይህን ሕግ ሁሉ ያደርግባታል። ሰውየውም ከኀጢአት ንጹሕ ይሆናል፤ ሴቲቱም ኀጢአቷን ትሸከማለች።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 5: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ