ሙሴም አላቸው፥ “ይህንስ እንዳላችሁት ብታደርጉ፥ ታጥቃችሁም በእግዚአብሔር ፊት ወደ ጦርነት ብትሄዱ፥ እርሱም ጠላቱ ከፊቱ እስኪጠፋ ድረስ ከእናንተ እያንዳንዱ ሰው የጦር መሣሪያውን ይዞ በእግዚአብሔር ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገር፥ ምድሪቱም በእግዚአብሔር ፊት ድል እስክትሆን ድረስ ከዚያም በኋላ ትመለሳላችሁ፤ በእግዚአብሔርም ፊት በእስራኤል ዘንድ ንጹሓን ትሆናላችሁ፤ ይህች ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ርስት ትሆናችኋለች። እንዲህ ባታደርጉ ግን፥ በእግዚአብሔር ፊት ትበድላላችሁ፤ ክፉ ነገር ባገኛችሁ ጊዜ በደላችሁን ታውቃላችሁ። ለልጆቻችሁ ከተሞችን፥ ለበጎቻችሁም በረቶችን ሥሩ፤ ከአፋችሁም የወጣውን ነገር አድርጉ።” የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆችም ሙሴን እንዲህ ብለው ተናገሩት፥ “እኛ አገልጋዮችህ ጌታችን እንዳዘዘ እናደርጋለን። ልጆቻችን ሚስቶቻችንም፥ እንሰሶቻችንም ሁሉ በዚያ በገለዓድ ከተሞች ይሆናሉ፤ እኛ አገልጋዮችህ ግን ሁላችን የጦር መሣሪያችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ጌታችን እንደ ተናገረ ወደ ጦርነት እንሄዳለን።” ሙሴም ካህኑን አልዓዛርን፥ የነዌንም ልጅ ኢያሱን፥ የእስራኤልንም ነገድ አባቶች አለቆች አዘዛቸው። ሙሴም፥ “የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች ሁላቸው የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ከእናንተ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ለጦርነት ዮርዳኖስን ቢሻገሩ፥ ምድሪቱንም ድል ብትነሡ ፥ የገለዓድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ትሰጡአቸዋላችሁ። የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ከእናንተ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ወደ ጦርነት ባይሻገሩ ግን ልጆቻቸውን፥ ሚስቶቻቸውን፥ ከብቶቻቸውንም በፊታችሁ ወደ ከነዓን ምድር ንዱአቸው፤ በከነዓን ምድር በእናንተ መካከል ርስታቸውን ይወርሳሉ” አላቸው። የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆችም መልሰው፥ “ጌታችን ለእኛ ለአገልጋዮችህ እንደ ተናገረ እንዲሁ እናደርጋለን። የጦር መሣሪያችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ወደ ከነዓን ምድር እንሻገራለን፤ ከዮርዳኖስም ማዶ የወረስነው ርስት ይሆንልናል” አሉት። ሙሴም ለጋድ ልጆችና ለሮቤል ልጆች፥ ለዮሴፍም ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ፥ የአሞሬዎናውያንን ንጉሥ የሴዎንን መንግሥት፥ የባሳንንም ንጉሥ የዐግን መንግሥት፥ ምድሪቱንም፥ ከተራሮችም ጋር ከተሞችን፥ በዙሪያቸውም ያሉትን የምድሪቱን ከተሞች ሰጣቸው። የጋድ ልጆች ዲቦንን፥ አጣሮትን፥ አሮዔርን፤ ሶፋንን፥ ኢያዜርን፥ ናምራን፥ ቤታራንን ሰባት የተመሸጉ ከተሞች አድርገው ሠሩ፤ አስረዘሙአቸውም፤ የበጎች በረቶችንም ሠሩ። የሮቤልም ልጆች ሐሴቦንን፥ ኤልያሌንን፥ ቂርያታይምን፤ በቅጥር የተከበቡ በኤልሜዎንንና፥ ሴባማን ሠሩ፤ እነዚህንም የሠሩአቸውን ከተሞች በየስማቸው ጠሩአቸው። የምናሴም ልጅ የማኪር ልጅ ወደ ገለዓድ ሄዶ ገለዓድን ያዘ፤ በእርስዋም የነበሩትን አሞሬዎናውያንን አጠፋ። ሙሴም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ገለዓድን ሰጠው፤ በእርስዋም ተቀመጠ። የምናሴም ልጅ ኢያዕር ሄዶ መንደሮችዋን ወሰደ፤ የኢያዕርም መንደሮች ብሎ ጠራቸው። ናባውም ሄዶ ቄናትንም፥ መንደሮችዋንም ወሰደ፤ በስሙም ናቦት ብሎ ጠራቸው።
ኦሪት ዘኍልቍ 32 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘኍልቍ 32:20-42
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች