እንጀራ መያዝም ረሱ፤ ለእነርሱም ከአንድ እንጀራ በቀር በታንኳይቱ አልነበራቸውም። እርሱም “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ፤” ብሎ አዘዛቸው። እርስ በርሳቸውም “እንጀራ ስለሌለን ይሆናል፤” ብለው ተነጋገሩ። ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው “እንጀራ ስለሌላችሁ ስለ ምን ትነጋገራላችሁ? ገና አልተመለከታችሁምን? አላስተዋላችሁምን? ልባችሁስ ደንዝዞአልን? ዐይን ሳላችሁ አታዩምን? ጆሮስ ሳላችሁ አትሰሙምን? ትዝስ አይላችሁምን? አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት መሶብ አነሣችሁ” እነርሱም “ዐሥራ ሁለት፤” አሉት። ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት ቅርጫት አነሣችሁ? እነርሱም “ሰባት” አሉት። “ገና አላስተዋላችሁምን?” አላቸው። ወደ ቤተ ሳይዳም መጡ። ዕውርም አመጡለት፤ እንዲዳስሰውም ለመኑት። ዕውሩንም እጁን ይዞ ከመንደር ውጭ አወጣው፤ በዐይኑም ተፍቶበት እጁንም ጭኖበት “አንዳች ታያለህን?” ብሎ ጠየቀው። አሻቅቦም “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አያለሁ፤” አለ። ከዚህም በኋላ ደግሞ እጁን በዐይኑ ላይ ጫነበት፤ አጥርቶም አየ፤ ዳነም፤ ከሩቅም ሳይቀር ሁሉን ተመለከተ። ወደ ቤቱም ሰደደውና “ወደ መንደሩ አትግባ፤ በመንደሩም ለማንም አንዳች አትናገር፤” አለው። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም በፊልጶስ ቂሣርያ ወዳሉ መንደሮች ወጡ፤ በመንገድም “ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ?” ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው። እነርሱም “መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ” ብለው ነገሩት። “እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም “አንተ ክርስቶስ ነህ፤” ብሎ መለሰለት። ስለ እርሱም ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ በሽማግሌዎችም በካህናት አለቆችም በጻፎችም ሊናቅ፥ ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር፤ ቃሉንም ገልጦ ይናገር ነበር። ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። እርሱ ግን ዘወር አለ፤ ደቀ መዛሙርቱንም አይቶ ጴጥሮስን ገሠጸውና “ወደ ኋላዬ ሂድ! አንተ ሰይጣን! የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና፤” አለ። ሕዝቡንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው “በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን ያድናታል። ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?
የማርቆስ ወንጌል 8 ያንብቡ
ያዳምጡ የማርቆስ ወንጌል 8
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 8:14-36
4 ቀናት
አመለካከትዎን መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው ቃል በማስተካከል 4ቱን ቀናት ያሳልፉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ በድል ለመጓዝ የእግዚአብሔርን አመለካከት እንዴት እንደጠበቁ ከተለያዩ ታሪኮች ይማሩ።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች