ማርቆስ 8:14-36

ማርቆስ 8:14-36 NASV

ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለ ረሱ፣ ከአንድ እንጀራ በቀር በጀልባ ውስጥ ምንም አልነበራቸውም። ኢየሱስም፣ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ብሎ አዘዛቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው፣ “እንዲህ የሚለን እኮ እንጀራ ስለሌለን ነው” ተባባሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት የምትነጋገሩት ስለ ምንድን ነው? አሁንም አታስተውሉምን? ልብ አትሉምን? ወይስ ልባችሁ ደንድኗል? ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙምን? አታስታውሱምን? ዐምስቱን እንጀራ ለዐምስት ሺሕ ሰው በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” እነርሱም፣ “ዐሥራ ሁለት” አሉት። “ሰባቱንስ እንጀራ ለአራት ሺሕ በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “ሰባት” አሉት። እርሱም፣ “እስከ አሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን?” አላቸው። ከዚያም ወደ ቤተ ሳይዳ መጡ፤ ጥቂት ሰዎችም አንድ ዐይነ ስውር ወደ ኢየሱስ አምጥተው እንዲዳስሰው ለመኑት። እርሱም የዐይነ ስውሩን እጅ ይዞ ከሰፈር ውጭ አወጣው፤ በዐይኖቹም ላይ እንትፍ ብሎበት፣ እጁንም በላዩ ጭኖ፣ “ምን የሚታይህ ነገር አለ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም ቀና ብሎ አይቶ፣ “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲንቀሳቀሱ አያለሁ” አለ። ኢየሱስም እንደ ገና እጆቹን በሰውየው ዐይኖች ላይ ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ዐይኖቹ በሩ፤ ብርሃኑም ተመለሰለት፤ ሁሉንም ነገር አጥርቶ ማየት ቻለ። ከዚያም፣ “ወደ መንደሩ አትግባ! በመንደሩም ለማንም አትናገር” ብሎ ወደ ቤቱ ሰደደው። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ ፊልጶስ ቂሳርያ መንደሮች ሄደ፤ በመንገድ ላይ ሳሉም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሰዎች እኔን ማን ነው ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “መጥምቁ ዮሐንስ የሚሉህ አሉ፤ ሌሎች ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው ነገሩት። ቀጥሎም፣ “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፣ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው። ኢየሱስም ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቃቸው። ከዚያም የሰው ልጅ ብዙ መከራ እንደሚቀበል፣ በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እንደሚናቅ፣ እንደሚገደል፣ ከሦስት ቀንም በኋላ እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር። እርሱም ይህን በግልጽ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን እያየ ጴጥሮስን፣ “አንተ ሰይጣን፤ ወደ ኋላዬ ሂድ! የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በሐሳብህ የለምና” በማለት ገሠጸው። ከዚህ በኋላ፣ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ለማዳን የሚወድድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል። ሰው ዓለሙ ሁሉ የርሱ ቢሆንና ነፍሱን ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል?

ተዛማጅ ቪዲዮዎች