የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማ​ር​ቆስ ወን​ጌል 12:13-27

የማ​ር​ቆስ ወን​ጌል 12:13-27 አማ2000

በንግግርም ሊያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑትን ወደ እርሱ ላኩ። መጥተውም “መምህር ሆይ! የሰውን ፊት ሳትመለከት በእውነት የእግዚአብሔር መንገድ ታስተምራለህና እውነተኛ እንደ ሆንህ ለማንምም እንዳታደላ እናውቃለን፤ ለቄሳር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? እንስጥን ወይስ አንስጥ?” አሉት። እርሱ ግን ግብዝነታቸውን አውቆ “ለምን ትፈትኑኛላችሁ? አየው ዘንድ አንድ ዲናር አምጡልኝ፤” አላቸው። እነርሱም አመጡለት። “ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት?” አላቸው፤ እነርሱም “የቄሳር ናት፤” አሉት። ኢየሱስም መልሶ “የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ፤” አላቸው። በእርሱም ተደነቁ። ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው ጠየቁት እንዲህም አሉት “መምህር ሆይ! ሙሴ “የአንድ ሰው ወንድም ሚስቱን ትቶ ልጅ ሳያስቀር ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ፤’ ብሎ ጻፈልን። ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ዘር ሳያስቀር ሞተ፤ ሁለተኛውም አገባት፤ ዘርም ሳይተው ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ ሰባቱም አገቡአት፤ ዘርም አላስቀሩም። ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች። ሰባቱ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀን ሲነሡ ከእነርሱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?” ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን? ከሙታንስ ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡምም። ስለ ሙታን ግን እንዲነሡ እግዚአብሔር ‘እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤’ እንዳለው በሙሴ መጽሐፍ በቍጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። እንግዲህ እጅግ ትስታላችሁ።”