ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስን በንግግሩ ለማጥመድ ወደ እርሱ ተላኩ። ቀርበውም እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፥ አንተ እውነተኛ መሆንህን እናውቃለን፤ ሰውንም በመፍራትና በይሉኝታ የምታደርገው ነገር የለም፤ የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት ታስተምራለህ፤ ታዲያ፥ ለሮም ንጉሠ ነገሥት ግብር መክፈል ሕጋዊ ነውን? ወይስ አይደለም? እንገብር ወይስ አንገብር?” ኢየሱስም ግብዝነታቸውን ዐውቆ፦ “ለምን ልታጠምዱኝ ትፈልጋላችሁ? እስቲ ገንዘቡን አምጡና አሳዩኝ፤” አላቸው። እነርሱም ገንዘቡን አመጡለት፤ እርሱም “በዚህ ገንዘብ ላይ ያለው መልክና የተጻፈው ስም የማን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “የሮም ንጉሠ ነገሥት ነው፤” አሉት። ኢየሱስም “እንግዲያውስ የንጉሡን ለንጉሡ፥ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ፤” ሲል መለሰላቸው። እነርሱም በመልሱ ተደነቁ። “የሙታን መነሣት የለም፤” የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ መጥተው፤ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፥ ‘አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ከሚስቱ በሞት ቢለይ ወንድሙ ሴትዮዋን አግብቶ ለሟቹ ዘር ይተካለት፤’ ብሎ ሙሴ ጽፎልናል። ታዲያ፥ ሰባት ወንድማማች ነበሩ፤ የሁሉም ታላቅ ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ሁለተኛውም ወንድሙ ያቺኑ ሴት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ ሆነ፤ በዚህ ሁኔታ ሰባቱም አግብተዋት ዘር ሳይተኩ ሞቱ፤ ከሁሉም በኋላ ደግሞ ሴትዮዋ ሞተች። ሰባቱም ወንድማማች በየተራ አግብተዋታልና እንግዲህ ሙታን በሚነሡበት ጊዜ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተ የምትሳሳቱት ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ባለማወቃችሁ አይደለምን? ሙታንስ ሲነሡ በሰማይ እንዳሉት መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡምም። ስለ ሙታን መነሣት የሆነ እንደ ሆነ ግን እግዚአብሔር ሙሴን ከቊጥቋጦው እሳት ውስጥ ምን እንደ ተናገረው ከሙሴ መጽሐፍ አላነበባችሁምን? ይኸውም ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብ አምላክ ነኝ፤’ ያለው ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ እናንተ ግን እጅግ ትሳሳታላችሁ።”
የማርቆስ ወንጌል 12 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 12:13-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos