የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትን​ቢተ ሚክ​ያስ 5

5
1የጭፍሮች ሴት ልጅ ሆይ፥ ጭፍሮችሽን አሁን ሰብስቢ፥ ከብቦ አስጨንቆናል፥ የእስራኤልን ፈራጅ ጕንጩን በበትር ይመታሉ።
2አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፥ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።
3ስለዚህ ወላጂቱ እስከምትወልድበት ጊዜ ድረስ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ የቀሩትም ወንድሞቹ ወደ እስራኤል ልጆች ይመለሳሉ።
4እርሱም ይቆማል፥ በእግዚአብሔርም ኃይል በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ግርማ መንጋውን ይጠብቃል፥ እነርሱም ይኖራሉ፥ እርሱ አሁን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ታላቅ ይሆናልና።
5ይህም ለሰላም ይሆናል፥ አሦራዊውም ወደ አገራችን በገባ ጊዜ፥ ምድራችንንም በረገጠ ጊዜ ሰባት እረኞችና ስምንት አለቆች እናስነሣበታለን።
6የአሦርንም አገር በሰይፍ፥ የናምሩድንም አገር በመግቢያው ውስጥ ያፈርሳሉ፥ አሦራዊውም ወደ አገራችን በገባ ጊዜ፥ ዳርቾቻችንንም በረገጠ ጊዜ እርሱ ይታደገናል።
7የያዕቆብም ቅሬታ በብዙ አሕዛብ መካከል ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚወርድ ጠል፥ በሣር ላይ እንደሚወርድ ካፊያ፥ ሰውንም እንደማይጠብቅ፥ የሰውንም ልጆች ተስፋ እንደማያደርግ ይሆናል።
8በዱር አራዊትም መካከል እንዳለ አንበሳ፥ በበጎች መንጋም መካከል አልፎ እንደሚረግጥ፥ የሚታደግም ሳይኖር እንደሚነጥቅ እንደ አንበሳ ደቦል፥ እንዲሁ የያዕቆብ ቅሬታ በአሕዛብና በብዙ ወገኖች መካከል ይሆናል።
9እጅህ በጠላቶችህ ላይ ከፍ ከፍ ትበል፥ ጠላቶችህም ሁሉ ይጥፉ።
10በዚያም ቀን ፈረሶችህን ከመካከልህ አጠፋለሁ፥ ሰረገሎችህንም እሰብራለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥
11የምድርህንም ከተሞች አጠፋለሁ፥ ምሽጎችህንም ሁሉ አፈርሳለሁ፥
12መተትንም ከእጅህ አጠፋለሁ፥ ምዋርተኞችም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆኑልህም፥
13የተቀረጹትን ምስሎችህንና ሐውልቶችህን ከመካከልህ አጠፋለሁ፥ ለእጅህም ሥራ ከእንግዲህ ወዲህ አትሰግድም፥
14የማምለኪያ ዐፀዶችህንም ከመካከልህ እነቅላለሁ፥ ከተሞችህንም አፈርሳለሁ።
15ባልሰሙም አሕዛብ ላይ በቍጣና በመዓት እበቀላለሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ