ትንቢተ ሚክያስ 3
3
1እንዲህም አልሁ፦ የያዕቆብ አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዦች ሆይ፥ እባካችሁ ስሙኝ፥ ፍርድን ታውቁ ዘንድ አይገባችሁምን?
2መልካሙን ጠልታችኋል፥ ክፉውንም ወድዳችኋል፥ ቁርበታቸውን ገፍፋችኋቸዋል፥ ሥጋቸውንም ከአጥንታቸው ለያይታችኋል፥
3የሕዝቤን ሥጋ በልታችኋል፥ ቁርበታቸውንም ገፍፋችኋቸዋል፥ አጥንታቸውንም ሰብራችኋል፥ ለአፍላል እንደሚሆን ሥጋ ለድስትም እንደሚሆን ሙዳ ቈራረጣችኋቸው።
4የዚያን ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ፥ እርሱም አይሰማቸውም፥ ሥራቸውንም ክፉ አድርገዋልና በዚያን ጊዜ ፊቱን ከእነርሱ ይሰውራል።
5እግዚአብሔር ሕዝቤን ስለሚያስቱ ነቢያት እንዲህ ይላል፥ በጥርሳቸው ሲነክሱ በሰላም ይሰብካሉ፥ በአፋቸው ግን አንዳች በማይሰጥ ሰው ላይ ሰልፍን ያስቡበታል።
6ስለዚህ ሌሊት ይሆንባችኋል እንጂ ራእይ አይሆንላችሁም፥ ጨለማም ይሆንባችኋል እንጂ አታምዋርቱም፥ ፀሐይም በነቢያት ላይ ትገባለች፥ ቀኑም ይጠቁርባቸዋል።
7ከእግዚአብሔርም ዘንድ መልስ የለምና ባለ ራእዩቹ ያፍራሉ፥ ምዋርተኞችም ይዋረዳሉ፥ ሁሉም ከንፈራቸውን ይሸፍናሉ።
8እኔ ግን በደሉን ለያዕቆብ፥ ኃጢአቱንም ለእስራኤል እነግር ዘንድ በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይልንና ፍርድን ብርታትንም ተሞልቻለሁ።
9ፍርድን የምትጠሉ ቅን ነገርንም ሁሉ የምታጣምሙ እናንተ የያዕቆብ ቤት አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዦች ሆይ፥ እባካችሁ ይህን ስሙ።
10ጽዮንን በደም፥ ኢየሩሳሌምንም በኃጢአት ይሠራሉ።
11አለቆችዋ በጉቦ ይፈርዳሉ፥ ካህናቶችዋም በዋጋ ያስተምራሉ፥ ነቢያቶችዋም በገንዘብ ያምዋርታሉ፥ ከዚህም ጋር፦ እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ክፉ ነገር ምንም አይመጣብንም እያሉ በእግዚአብሔር ይታመናሉ።
12ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፥ ኢየሩሳሌም የድንጋይ ክምር ትሆናለች፥ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል።
Currently Selected:
ትንቢተ ሚክያስ 3: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ