የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 25:14-40

የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 25:14-40 አማ2000

“ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ዐቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት፤ ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው። አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ ‘ጌታ ሆይ! አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት፤’ አለ። ጌታውም ‘መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፥ በጥቂቱ ታምነሃል፤ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ፤’ አለው። ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት፤’ አለ። ጌታውም ‘መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፤ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ፤’ አለው። አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ፤’ አለ። ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው ‘አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፤ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር። ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት ዐሥር መክሊትም ላለው ስጡት፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፤ ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።’ “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፤ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል። ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል ‘እናንተ የአባቴ ቡሩካን! ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፤ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፤ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፤ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፤ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና።’ ጻድቃንም መልሰው ይሉታል ‘ጌታ ሆይ! ተርበህ አይተን መቼ አበላንህ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን?’ ንጉሡም መልሶ ‘እውነት እላችኋለሁ፤ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት፤’ ይላቸዋል።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች