የሉቃስ ወንጌል 14
14
ሆዱ የተነፋውን ሰው እንደ ፈወሰ
1ከዚህም በኋላ ሄዶ ከፈሪሳውያን አለቆች ወደ አንዱ ቤት በሰንበት ቀን እህል ሊበላ ገባ፤ እነርሱ ግን ይጠባበቁት ነበር። 2እነሆም፥ ሆዱ የተነፋ አንድ ሰው በፊቱ ነበር። 3ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ሕግ ዐዋቂዎችንና ፈሪሳውያንን፥ “በሰንበት ድውይ መፈወስ ይገባልን? ወይስ አይገባም?” ብሎ ጠየቃቸው። 4እነርሱም ዝም አሉ፤ ይዞም ፈወሰውና ሰደደው። 5#ማቴ. 12፥11። “ከእናንተ በሬው ወይም አህያው በጕድጓድ ውስጥ የወደቀበት አንድ ሰው ቢኖር ዕለቱን በሰንበት ቀን ያነሣው የለምን?” አላቸው። 6ስለዚህም ነገር ሊመልሱለት አልተቻላቸውም።
በራስጌ መቀመጥን ስለሚወዱ ሰዎች
7በምሳ ላይ ለነበሩትም ወደ ላይኛው ወንበር ሲሽቀዳደሙ ባያቸው ጊዜ ምሳሌ መስሎ አስተማራቸው። 8እንዲህም አለ፥ “ለምሳ#በግሪኩ “ለሰርግ” ይላል። የጠራህ ሰው ቢኖርና ብትሄድ በላይኛው መቀመጫ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ የሚበልጥ ይመጣ ይሆናል። 9በኋላ ያ አንተንም እርሱንም የጠራ መጥቶ፦ ይህን ቦታ ለእርሱ ተውለት ይልሃልና፤ ያንጊዜም አፍረህ ትመለሳለህ፤ ወደ ዝቅተኛ ቦታም ትወርዳለህ። 10የጠራህ ሰው ቢኖርና ብትሄድ ግን የጠራህ በመጣ ጊዜ ወዳጄ ወደ ላይኛው መቀመጫ ውጣ ይልህ ዘንድ በታችኛው መቀመጫ ተቀመጥ፤ ያንጊዜም ከአንተ ጋር ለማዕድ በተቀመጡት ሰዎች ፊት ክብር ይሆንልሃል። 11#ማቴ. 23፥12፤ ሉቃ. 18፥14። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም ያሚያዋርድ ከፍ ይላልና።”
12የጠራውንም እንዲህ አለው፥ “በበዓል ምሳ ወይም ራት በምታደርግበት ጊዜ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን፥ ዘመዶችህንና ጎረቤቶችህን፥ ባለጸጎች ባልንጀሮችህንም አትጥራ፤ እነርሱም ይጠሩሃልና፤ ብድርም ይሆንብሃልና። 13ነገር ግን በበዓል ምሳ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን፥ ዕውሮችን፥ እጅና እግርም የሌላቸውን ጥራ። 14አንተም ብፁዕ ትሆናለህ፤ የሚከፍሉህ የላቸውምና፤ ነገር ግን ጻድቃን በሚነሡበት ጊዜ ዋጋህን ታገኛለህ።” 15ለምሳ ከተቀመጡትም አንዱ ይህን ሰምቶ፥ “በእግዚአብሔር መንግሥት እህል የሚበላ ብፁዕ ነው” አለው።
ለምሳ ስለ መጠራት
16ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “አንድ ሰው ታላቅ ምሳ#በግሪኩ “ራት” ይላል። አደረገና ብዙ ሰዎችን ጠራ። 17ለምሳ የተጠሩበትም ቀን በደረሰ ጊዜ የታደሙትን ይጠራቸው ዘንድ አገልጋዩን ላከ፤ እርሱም ሄዶ የታደሙትን፦ አሁን ምሳውን ፈጽመን አዘጋጅተናልና ኑ አላቸው። 18ሁሉም በአንድ ቃል ተባብረው እንቢ አሉ፤ የመጀመሪያው፦ እርሻ ገዝችአለሁ፤ ሄጄም ላያት እሻለሁ፤ እንቢ እንደ አላልሁ ቍጠርልኝ በለው አለው። 19ሁለተኛውም፦ አምስት ጥማድ በሬ ገዝቻለሁ፤ ላያቸውና ልፈትናቸው እሄዳለሁ፤ እንደ መጣሁ፥ እንቢ እንደ አላልሁም ቍጠርልኝ በለው አለው። 20ሦስተኛውም፦ ሚስት አግብችአለሁ፤ ስለዚህ ልመጣ አልችልም በለው አለው። 21አገልጋዩም ተመልሶ ለጌታው ይህንኑ ነገረው፤ ያንጊዜም ባለቤቱ ተቈጣ፤ አገልጋዩንም፦ ፈጥነህ ወደ አደባባይና ወደ ከተማው ጐዳና ሂድ፤ ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን፥ ዕውሮችንና አንካሶችን ወደዚህ አምጣልኝ አለው። 22ከዚህም በኋላ አገልጋዩ፦ አቤቱ እንደ አዘዝኸኝ አደረግሁ፤ ገናም ቦታ አለ አለው። 23ጌታውም አገልጋዩን፦ ወደ መንገዶችና ወደ ከተማው ቅጥር ፈጥነህ ሂድና ቤቴ እንዲመላ ይገቡ ዘንድ ግድ በላቸው አለው። 24ከእነዚህ ከታደሙት ሰዎች አንዱ ስንኳን ማዕዴን#በግሪኩና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “ራቴን” ይላል። እንደማይቀምሳት እነግራችኋለሁ።”
ጌታን ስለ መከተል
25ከዚህም በኋላ ብዙ ሰዎች አብረውት ሲሄዱ መለስ ብሎ እንዲህ አላቸው። 26#ማቴ. 10፥37። “ወደ እኔ የሚመጣ፥ ሊከተለኝም የሚወድ አባቱንና እናቱን፥ ሚስቱንና ልጆቹን፥ ወንድሞቹንና እኅቶቹን፥ የራሱንም ሰውነት እንኳ ቢሆን የማይጠላ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። 27#ማቴ. 10፥38፤ 16፥24፤ ማር. 8፥34፤ ሉቃ. 9፥23። መስቀሉን ተሸክሞ ሊከተለኝ የማይመጣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።”
ቤት ስለሚሠራው ሰው ምሳሌ
28“ከእናንተም ወገን የግንብ ቤት መሥራት የሚወድ ቢኖር ይጨርሰው ዘንድ የሚችል እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ የሚፈጅበትን የማያስብ ማን ነው? 29መሠረቱን ጥሎ መጨረስ ያቃተውም እንደ ሆነ ያዩት ሁሉ፥ 30‘ይህ ሰው ሊሠራ ጀመረ፤ ግን መጨረስ ተሳነው’ እያሉ ሊዘብቱበት ይጀምራሉ። 31ንጉሥም ሌላውን ንጉሥ ይወጋ ዘንድ ሊሄድ ቢወድ ሁለት እልፍ ይዞ ወደ እርሱ የሚመጣውን በአንድ እልፍ ሊዋጋው ይችል እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ይመክር የለምን? 32ያለዚያ ግን፥ ገና በሩቁ ሳለ አማላጆች መልእክተኞችን ልኮ ዕርቅ ይለምናል። 33እንግዲህ እንደዚሁ ከእናንተ ወገን ከሁሉ ያልወጣ፥ የእርሱ ገንዘብ ከሆነውም ሁሉ ያልተለየ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።
34“ጨው መልካም ነው፤ ጨው አልጫ ከሆነ እንግዲህ በምን ያጣፍጡታል? 35ለምድርም ቢሆን፥ ለፍግ መቆለያም ቢሆን አይረባም፤ ነገር ግን ወደ ውጭ ይጥሉታል፤ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።”
Currently Selected:
የሉቃስ ወንጌል 14: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ