ተረፈ ኤርምያስ 1
1
1እግዚአብሔር ያዘዘውን ይነግሯቸው ዘንድ የባቢሎን ንጉሥ ማርኮ ወደ ባቢሎን ወደ ወሰዳቸው ሰዎች ኤርምያስ የላከው መጽሐፍ ግልባጭ ይህ ነው። 2እግዚአብሔርን ስለ በደላችሁበት ኀጢአታችሁ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ምርኮኞች አድርጎ ወደ ባቢሎን ይወስዳችኋል። 3እንዲሁም ወደ ባቢሎን ገብታችሁ እስከ ሰባተኛ ትውልድ ለብዙ ዓመታት፥ ለረዥም ወራትም በዚያ ትኖራላችሁ። ከዚህ በኋላ ግን ከዚያ ቦታ በሰላም አወጣችኋለሁ።
4አሁን ግን የብርና የወርቅ፥ የእንጨትም የሆኑ ጣዖቶችን በባቢሎን ታያላችሁ ፤ በጫንቃቸውም ይሸከሟቸዋል፤ አሕዛብንም ያስፈሯቸዋል። 5እንግዲህ እንደ ሌሎች እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ፤ ስለ እነርሱም ፍርሀት አይደርባችሁ። 6በፊታቸውና በኋላቸው ሆነው ሲሰግዱላቸው አሕዛብን ብታዩ፥ በልባችሁ፥ “አቤቱ ስግደት ለአንተ ይገባል” በሉ። 7መልአኬ ከእናንተ ጋር ይኖራልና፥ ለሰውነታችሁም ይጠነቀቃልና።
8ጃንሸላሚ የሠራው አንደበት አላቸው፤ ይኸውም የወርቅና የብር ነው፤ እነርሱም ሐሰት ናቸው፤ መናገርም አይችሉም። 9ጌጥ ለምትወድ ድንግል እንደሚያደርጉ ወርቅን ወስደው፥ በጣዖቶቻቸው ራስ ላይ አክሊል አደረጉ። 10ከእነርሱም ካህናቱ ወርቁንና ብሩን እየወሰዱ ለመፍቅዳቸው የሚያውሉበት ጊዜ ነበረ። 11ከእርሱም በቤታቸው ለነበሩ አመንዝራዎች ይሰጧቸው ነበር። የብር፥ የወርቅና የእንጨት ጣዖቶቻቸውንም እንደ ሰው በልብስ ያስጌጧቸው ነበር። 12ዝገታቸውንም ከራሳቸው አያርቁም ነበር። 13በነጭ ሐር ይሸፍኗቸው ነበር፤ በላያቸውም እጅግ ብዙ ከሆነው የቤት ትቢያ የተነሣ ይወለውሏቸው ነበር። 14እንደ ፈራጅ ሰውም በትር ያስይዟቸዋል፤ ነገር ግን የሚገፋቸውን አይበቀሉትም። 15በእጁ ሰይፍና ምሳር አለ፤ ራሱንም ከጦርነትና ከሌቦች አያድንም፤ 16አማልክትም እንዳይደሉ በዚህ ይታወቃሉ፤ እንግዲህ አትፍሩአቸው። 17የተሰበረ የሸክላ ዕቃ እንደማይጠቅም ጣዖቶቻቸው እንዲሁ ናቸው። በቤትም ይቸነክሯቸዋል፤ ከሚገባውም የሰው እግር የተነሣ ትቢያ በዐይናቸው ይሞላል። 18ንጉሥን በበደለ ሰው ላይ በሮች እንደሚዘጉበት፥ በመቃብር ውስጥ ያለ ሟችም እንደሚዘጋበት እንዲሁ ሌቦች እንዳይሠርቋቸው ካህናቶቻቸው በመዝጊያና በቅWልፍ ይጠብቋቸዋል።
19መብራት ያበሩላቸዋል፤ የሚያዩትም የለም። 20በቤት ውስጥ እንዳለ ምሰሶ ናቸው፤ የሆድ ዕቃቸውን የምድር አራዊት እንደሚበሏቸው ይናገራሉ፤ እነርሱንና ልብሳቸውን ሲበሏቸው እነርሱ አያውቁም። 21በቤተ ጣዖቱ ከሚጤሰው ጢስ የተነሣ ፊታቸው ይጠቍራል። 22በአካላቸውና በራሳቸውም ላይ የሌሊት ወፍ፥ ወፎችና ድመት ይቀመጣሉ። 23በዚህም እነርሱ አማልክት እንዳይደሉ ታውቃላችሁ፤ እንግዲህ ወዲህ አትፍሩአቸው።
24ወርቅ ቢያስቀምጡት ካልወለወሉት እንደማያበራ አያበሩም፤ ቀጥቅጠው ሲሠሯቸውም አያውቁም። 25በከፍተኛ ዋጋ ገዟቸው፤ ነገር ግን እስትንፋስ የላቸውም። 26እግር የላቸውም፤ ድካማቸውም ይታወቅ ዘንድ በትከሻቸው ይሸከሟቸዋል፤ 27የሚያመልኳቸው ያፍራሉ፤ በምድርም ላይ ቢወድቁ ራሳቸው አይነሡም፤ ቢያነሡአቸውም ራሳቸው አይቆሙም፤ ቢያዘነብሉም ራሳቸው በራሳቸው ቀጥ አይሉም፤ ለእነርሱም መሥዋዕት ማቅረብ ለሞተ ሰው ምግብ እንደ ማቅረብ ነው።
28ካህናቶቻቸውም መሥዋዕታቸውን እየሸጡ ያቃልሏቸዋል። እንደዚሁም ሚስቶቻቸው መሥዋዕቱን ያጣፍጣሉ፤ ነገር ግን ከእርሱ ለበሽተኛና ለድሃ አይሰጡም። 29አራሶችና የተዳደፉ ሴቶችም ከመሥዋዕቱ ይነካሉ፤ በዚህም አማልክት እንዳይደሉ ዕወቁ፤ እንግዲህ አትፍሩአቸው። 30ሴቶች ከብር ከወርቅና ከእንጨት ለተሠሩ አማልክት መሥዋዕት ካቀረቡላቸው በምን አማልክት ይባላሉ? 31ካህናቶቻቸውም በጣዖታቱ ቤት ያድራሉ፤ ልብሳቸው የተቀደደ ነው፤ ራሳቸውም ጢማቸውም የተላጨ ነው፤ ራሳቸውም ግልጥ ነው። 32በሙት መታሰቢያ ላይ እንደሚደረግ በአማልክቶቻቸው ፊት እየጮኹ ያለቅሳሉ።
33ካህናቶቻቸውም ልብሶቻቸውን ገፍፈው ለሚስቶቻቸውና ለልጆቻቸው ያለብሳሉ። 34ክፉ ያደረገባቸው፥ ወይም መልካምን ያደረገላቸው ሰው ቢኖር ብድራቱን አይከፍሉትም፤ አያነግሡም፤ አይሽሩምም። 35እንዲሁም አያበለጽጉም፤ አያደኸዩምም፤ ስእለት ተስሎ ያልሰጠ ቢኖርም አይፈላለጉትም። 36ሰውን ከሞት አያድኑም፤ ደካማውንም ከኀይለኛው አያድኑም። 37ዕውር አያበሩም፤ ሰውን ከችግሩ አያነሡትም። 38ለመበለቶች አይራሩም፤ ለድሃ-አደጉም በጎ አያደርጉም።
39አማልክቶቻቸው ከተራራ የተፈነቀሉ ድንጋዮችን ይመስላሉ፤ ከእንጨት፥ ከወርቅና ከብር የተቀረፁ ናቸው። የሚያመልኳቸውም ያፍራሉ። 40በምን ይመሰላሉ? ከለዳውያን ራሳቸው ሲንቋቸው እንግዲህ እንዴት አማልክት ይባላሉ? 41እነዚህ መናገር የማይችል ዲዳን ባዩ ጊዜ እርሱ መስማት እንደሚችል ይናገር ዘንድ እየለመኑት ወደ ቤል ያመጡታል። 42መስማትን እንደማይችሉ የሚያውቁ እነዚያም ሊያርቋቸው አይችሉም። 43ሴቶችም ወገባቸውን በመቀነት ታጥቀው በመንገድ ይቀመጣሉ፤ የእህል ቍርባንም ያቀርባሉ። 44ከእነርሱም አንዲቱ መንገድ ዐላፊውን ብታስተውና አብራው ብትተኛ፥ እንደ እርስዋ ዝግጁ ሆና አልተገኘችምና፥ መቀነቷም አልተፈታላትምና ይህችኛዋ ሌላዋን ትነቅፋታለች። ለእነርሱ የሚደረገው ሁሉ ሐሰት ነው፤ እንደ አማልክት ሊቈጥሯቸው፥ አማልክትም ሊሉአቸው እንዴት ይቻላል?
45ጠራቢዎችና አንጥረኞች ሠርተዋቸዋል፤ እነዚህም ጠራቢዎች ከፈቀዱት ውጭ አልሆኑም። 46የሠሯቸው አንጥረኞች ራሳቸውም ለብዙ ዘመን አይኖሩም። እንግዲህ በእነርሱ የተሠሩ እነዚህ እንዴት ለዘለዓለም ይኖራሉ? 47በኋላ ለሚመጡም ከንቱነትንና ስድብን ተዉ። 48ጦርነትና ጥፋት በመጣባቸው ጊዜ ካህናቶቻቸው ከእነርሱ ጋር ይሸሸጉ ዘንድ እርስ በርሳቸው ይመካከራሉ። 49እንግዲህ ራሳቸውን ከጦርነትና ከጥፋት የማያድኑ እንዴት አማልክት ናቸው? 50እነርሱ በወርቅና በብር የተለበጡ እንጨቶች ናቸውና፤ በኋላም ከንቱ መሆናቸው ይታወቃል። 51እነርሱም የሰው እጅ ሥራ እንጂ አማልክት እንዳልሆኑ፥ የአምላክነት ሥራም እንደሌላቸው ለአሕዛብና ለነገሥታት ሁሉ በግልጥ ይታወቃሉ።
52አማልክት እንዳይደሉ የማያውቅ ማን ነው? 53በሀገር ላይ ንጉሥን አያስነሡም፤ ለሰውም ዝናምን አይሰጡም። 54ለራሳቸው ፍርድን አይፈርዱም፤ ግፍንም አያርቁም፤ ምንም ማድረግ አይችሉምና፥ በሰማይና በምድር መካከል እንደሚበርሩ ቍራዎች ናቸው።
55ከእንጨት፥ ወይም ከወርቅ፥ ወይም ከብር የተሠሩ ጣዖታት ቤት ቢቃጠል፥ ካህናቶቻቸው ሸሽተው ራሳቸውን ያድናሉ፤ እነርሱ ግን እንደ ምሰሶ በመካከል ይቃጠላሉ። 56ንጉሥንም ቢሆን፥ ጠላትንም ቢሆን አይቃወሙም፤ እንግዲህ እንዴት አማልክት ናቸው? 57ከእንጨት፥ ከብርና ከወርቅ የተሠሩት ጣዖታት ከሌቦችና ከቀማኞች ራሳቸውን አያድኑም። 58የሚበረታቱባቸውም ወርቃቸውንና ብራቸውን፥ የተሸፈኑበትንም ልብሶች ይገፉአቸዋል፤ ይዘውም ይሄዳሉ፤ እነርሱ ግን ራሳቸውን እንኳ አይረዱም።
59ስለዚህ ከሐሰት አማልክት ይልቅ በኀይሉ የሚመካ ንጉሥ፥ ወይም በቤት ውስጥ የሚጠቅም፥ የገዛውም የሚገለገልበት ሸክላ ይሻላል፤ ወይም በቤት ውስጥ ያለውን ሁሉ የሚያድን መዝጊያ ከሐሰት አማልክት ይልቅ ይሻላል፤ በነገሥታት አዳራሽ ውስጥ ያሉ የእንጨት ምሰሶዎችም ከሐሰት አማልክት ይልቅ ይሻላሉ።
60ፀሐይና ጨረቃ፥ ከዋክብትም ብርሃን ናቸውና፥ ለጥቅምም ይላካሉና ይታዘዛሉ። 61እንደዚሁም መብረቅ በሚበርቅበት ጊዜ ከሩቅ ይታያል፤ እንደዚሁም ነፋስ በሀገሩ ሁሉ ይነፍሳል። 62ደማናትም በዓለሙ ሁሉ ይገለባበጡ ዘንድ ከእግዚአብሔር ታዝዘዋልና ትእዛዛቸውን ይፈጽማሉ። 63ተራሮችንና ዛፎችን ያቃጥል ዘንድ ከላይ የተላከ እሳትም የታዘዘውን ይፈጽማል፤ እነዚያ ግን በመልካቸውም፥ በኀይላቸውም እነዚህን አይመሳሰሉአቸውም።
64ስለዚህ እንደ አማልክት አይቈጠሩም፤ አማልክትም አይባሉም፤ ለሰው ፍርድ ማድረግን ወይም መልካም ማድረግን አይችሉምና። 65አማልክት እንዳይደሉ እንዲህ ዐውቃችኋቸዋልና አትፍሯቸው። 66ነገሥታትን አይረግሙም፤ አይመርቁምም። 67በሰማይም ለአሕዛብ ምልክትን አያሳዩም፤ እንደ ፀሐይና ጨረቃም አያበሩም። 68ከእነዚህ ይልቅ ወደ መጠጊያ መሸሽ የሚችሉና ራሳቸውን የሚያድኑ አራዊት ይሻላሉ። 69አማልክት እንደ ሆኑ በማናቸውም መንገድ እንደዚህ አልተገለጠልንምና ስለዚህ አትፍሩአቸው።
70በዱባ እርሻ ውስጥ ከአለ ማስፈራሪያ ምንም ምን እንደማይጠበቅ ከእንጨት የተሠሩና በወርቅና በብር የተለበጡ ጣዖቶቻቸው እንደዚሁ ናቸው። 71እንዲሁም በላዩ አዕዋፍ የሚቀመጡበትን፥ በአትክልት ቦታ ውስጥ ያለ ነጭ እሾህን ይመስላሉ፤ ከእንጨት የተሠሩ፥ በብርና በወርቅ የተለበጡ ጣዖቶቻቸው እንዲሁ በጨለማ ውስጥ እንደ ተጣለ በድን ናቸው። 72በላያቸው ከሚያረጁት ከቀይ ሐር ልብስና ከቀጭን ልብስ የተነሣ አማልክት እንዳይደሉ ታውቃላችሁ፤ በኋላም እነርሱ ራሳቸው ይጠፋሉ፤ ለሀገርም መሰደቢያ ይሆናሉ፤ 73ስለዚህ ጣዖት የሌለው፥ ከስድብም የራቀ ሰው ይሻላል።
Currently Selected:
ተረፈ ኤርምያስ 1: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ