ኦሪት ዘሌዋውያን 6
6
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2“ሰው ኀጢአትን ቢሠራ፥ የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ቸል ቢል፥ ያኖረበትን አደራ ወይም የኅብረትን ገንዘብ ወስዶ ባልንጀራውን ቢክድ፥ ወይም ቢቀማ፥ ወይም በባልንጀራው ላይ ግፍ ቢሠራ፥ 3ወይም የጠፋውን ነገር ቢያገኝ፥ ስለዚህም ቢዋሽ፥ ሰው ኀጢአትን ለመሥራት ከሚያደርጋቸው ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ በአንዲቱ በሐሰት ቢምል፥ 4እርሱ ቢበድልና ከዚህ በኋላ ንስሓ ቢገባ፥ በቅድሚያ የወሰደውን፥ ወይም በዐመፅና በግፍ የተቀበለውን፥ ወይም የተሰጠውን አደራ፥ ወይም ጠፍቶ ያገኘውን፥ 5ወይም በሐሰት የማለበትን ነገር ቢመልስ፥ በሙሉ ይመልስ፤ ከዚያም በላይ አምስተኛውን ክፍል ጨምሮ የበደሉን መሥዋዕት በሚያቀርብበት ቀን#ግእዙ “በዕለተ ዘለፍዎ” ይላል። ለባለ ገንዘቡ ይስጠው። 6ስለ በደል መሥዋዕትም ከመንጋው ነውር የሌለበትን፥ ዋጋው እንደ በደሉ የተገመተውን አውራ በግ ለእግዚአብሔር ያምጣ።#ዕብ. “ስለ በደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ከመንጋው ነውር የሌለበትን አውራ በግ እንደ ግምጋሜህ መጠን ስለ በደል መሥዋዕት ወደ ካህኑ ያምጣ” ይላል።። 7ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፤ ስለዚያም ስለ አደረገው በደል ሁሉ ይቅር ይባልለታል።”
ስለሚቃጠል መሥዋዕት ሕግ
8እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 9“አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ የሚቃጠለው የመሥዋዕቱ ሕግ ይህ ነው፤ የመሠዊያው እሳት በላዩ እየነደደች እስኪነጋ ትተዉታላችሁ። 10ካህኑም የተልባ እግር ቀሚስና የተልባ እግር ሱሪ በሰውነቱ ላይ ይለብሳል፤ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እሳቱ ከበላው በኋላ አመዱን አንሥቶ በመሠዊያው አጠገብ ያፈስሰዋል። 11ልብሱንም ያወልቃል፤ ሌላም ልብስ ይለብሳል፤ አመዱንም ተሸክሞ ከሰፈሩ ንጹሕ ወደ ሆነ ስፍራ ወደ ውጭ ያወጣዋል። 12እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል፤ አይጠፋም፤ ካህኑም ማለዳ ማለዳ ዕንጨት ያቃጥልበታል፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በዚያ ላይ ይረበርባል፤ በዚያም የደኅንነትን መሥዋዕት ስብ ያቃጥላል። 13ዘወትር በመሠዊያው ላይ እሳት ይነድዳል፤ አይጠፋም።
ስለ እህል ቍርባን
14“የአሮን ልጆች በእግዚአብሔር ፊት በመሠዊያው ፊት ለፊት የሚያቀርቡት የመሥዋዕት#ዕብ. “የእህል ቍርባን” ይላል። ሥርዐት ይህ ነው። 15ካህኑም ከእህሉ ቍርባን መልካሙን የስንዴ ዱቄት ከዘይት ጋር እፍኝ ሙሉ፥ ደግሞም በእህሉ ቍርባን ላይ ያለውን ዕጣን ሁሉ ያነሣል፤ ለእግዚአብሔርም በጎ መዓዛ ያለው የመታሰቢያ ቍርባን እንዲሆን ለመታሰቢያ ነውና በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል። 16ከእርሱም የተረፈውን አሮንና ልጆቹ ይበሉታል፤ ቂጣ ሆኖ በተቀደሰው ስፍራ ይበላል፤ በምስክሩ ድንኳን ዙሪያ ባለው አደባባይ ይበሉታል። 17በእርሾ ቦክቶ አይጋገርም። ከእግዚአብሔር መሥዋዕት የሰጠኋቸው ዕድል ፈንታ ይህ ነው፤ እርሱም እንደ ኀጢአትና እንደ በደል መሥዋዕት ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 18ከካህናት ወገን ወንድ ሁሉ ይበላዋል፤ በዘመናችሁ ለዘለዓለም ሕግ ነው። ከሚቃጠለው የእግዚአብሔር መሥዋዕት የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።”
19እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 20“እርሱን በቀባህበት ቀን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት የአሮንና የልጆቹ መባ ይህ ነው። የኢፍ መስፈርያ ዐሥረኛ ክፍል መልካሙን ዱቄት እኩሌታውን በጥዋት፥ እኩሌታውንም በማታ ለዘወትር መሥዋዕት ያቀርባሉ። 21ከዘይት ጋር በምጣድ ላይ ያደርጉታል፤ ለውሰውም ያገቡታል፤ ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን የሚፈተት መሥዋዕት ነው። 22ከልጆቹም በእርሱ ፋንታ የተቀባው ካህን ያቀርበዋል። ለዘለዓለም ሥርዐት ነው፤ ሁልጊዜም ይደረጋል። 23ካህናትም የሚያቀርቡት የእህል ቍርባን ሁሉ ፈጽሞ ይቃጠላል፤ ከእርሱም አንዳች አይበላም።”
ስለ ኀጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት
24እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 25“አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ የኀጢአት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኀጢአቱ መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ይታረዳል፤ እርሱም ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 26የሚሠዋው ካህን ይበላዋል፤ በምስክሩ ድንኳን ዙሪያ በአለው አደባባይ በተቀደሰ ስፍራ ይበሉታል። 27ሥጋውን የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል፤ ማናቸውም ልብስ ደም ቢረጭበት የተረጨበትን በተቀደሰ ስፍራ ያጥቡታል። 28የሚቀቀልበትን ሸክላ ይሰብሩታል፤ በናስም ዕቃ ቢቀቀል ይፈገፍጉታል፤ በውኃም ያጥቡታል። 29ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከእርሱ ይበላል፤ እርሱም ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 30ነገር ግን በመቅደሱ ውስጥ ለማስተስረያ ይሆን ዘንድ ከደሙ ወደ ምስክሩ ድንኳን የሚገባው የኀጢአት መሥዋዕት ሁሉ አይበላም፤ በእሳት ይቃጠላል።#በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 6 ከቍ. 31 እስከ 40 ያለው በዕብ. እና በግእዝ ምዕ. 7 ከቍ. 1 እስከ 10 ነው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 6: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ