ኦሪት ዘሌዋውያን 11
11
ስለሚበሉና ስለማይበሉ እንስሳት
(ዘዳ. 14፥3-21)
1እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 2“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብላችሁ ንገሩአቸው፦ በምድር ካሉት እንስሳት ሁሉ የምትበሉአቸው እንስሳት እነዚህ ናቸው። 3የተሰነጠቀ ሰኰና ያለውንና የሚያመሰኳውን እንስሳ ሁሉ ብሉ። 4ነገር ግን ከሚያመሰኩት ፥ ሰኰናቸውም ስንጥቅ ከሆነው ከእነዚህ አትበሉም፤ ግመል ያመሰኳል፤ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ለእናንተ ርኩስ ነው። 5ጥንቸል ያመሰኳል፤ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ይህ ለእናንተ ርኩስ ነው። 6ሽኮኮ ያመሰኳል፤ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ለእናንተ ርኩስ ነው። 7እርያም ሰኰናው ተሰንጥቆአል፤ ነገር ግን ስለማያመሰኳ ለእናንተ ርኩስ ነው። 8የእነዚህን ሥጋ አትበሉም፤ በድናቸውንም አትነኩም፤ ለእናንተ ርኩሳን ናቸው።
9“በውኃ ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ እነዚህን ትበላላችሁ፤ በውኆች፥ በባሕሮችም፥ በወንዞችም ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ትበላላችሁ። 10በውኆች ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ፥ በውኆች ውስጥ የሕይወት ነፍስ ከአላቸው ሁሉ፥ በባሕሮችና በወንዞች ውስጥ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፉ ናቸው። 11በእናንተም ዘንድ የተጸየፉ ይሆናሉ። ሥጋቸውንም አትበሉም፤ በድናቸውንም ትጸየፋላችሁ። 12ክንፍና ቅርፊትም የሌላቸው በውኃ ውስጥ የሚኖሩት ሁሉ ለእናንተ ርኩሳን ናቸው።
13“ከወፎችም ወገን የምትጸየፉአቸው እነዚህ ናቸው፤ አይበሉም፤ የተጸየፉ ናቸው፤ ንስር፥ ገዴ አሞራ፥ ዓሣ አውጭ፥ 14ጭላት፥ ጭልፊት፥ አንጭ አሞራ በየወገኑ፤ 15ቁራ ሁሉ በየወገኑ፤ 16ሰጎን በየወገኑ፤ ጠለቋ፥ ዝዪ፥ በቋል በየወገኑ፤ 17ጉጉት፥ እርኩም፥ ጋጋኖ፥ 18የውኃ ዶሮ፥ ይብራ፥ ጥምብ አንሣ አሞራ፥ 19ሸመላ፥ ሳቢሳ በየወገኑ፤ ጅንጅላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ።
20“የሚበርርም፥ በአራት እግሮችም የሚሄድ ተንቀሳቃሽ ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ነው። 21ነገር ግን ከሚበርሩት፥ አራትም እግሮች ካሉአቸው፥ ከእግሮቻቸውም በላይ በምድር ላይ የሚዘልሉባቸው ጭኖች ካሉአቸው ተንቀሳቃሾች እነዚህን ትበላላችሁ፤ 22ከእነርሱም እነዚህን አትበሉም፤ ኩብኩባ የሚመስለውም፥ ፌንጣ የሚመስለውም፥ አሸን የሚመስለውም፥ አንበጣ የሚመስለውም።#ምዕ. 11 በቍ. 22 የተገለጹት በዕብ. እና በግሪክ ሰባ. ሊ. “የሚበሉ ናቸው” 23የሚበርር፥ አራትም እግሮች ያሉት ተንቀሳቃሽ ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ነው።
24“በእነዚህም ርኩስ ትሆናላችሁ፤ የእነርሱንም በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 25ከእነርሱም በድን የሚያነሣ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 26ሰኰናም ያለው፥ ነገር ግን ሰኰናው ያልተሰነጠቀ፥ የማያመሰኳም እንስሳ ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ነው፤ እርሱን የሚነካ ሁሉ ርኩስ ነው። 27በአራት እግሮቹ ከሚሄድ እንስሳ ሁሉ በመዳፎቹ ላይ የሚሄድ ለእናንተ ርኩስ ነው፤ የእርሱን በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 28በድናቸውንም የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፤ እስከ ማታም ርኩስ ነው። እነርሱም በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው።
29“በምድር ላይም ከሚንቀሳቀስ ተንቀሳቃሽ እነዚህ ለእናንተ ርኩሳን ናቸው፤ ሙጭልጭላ፥ አይጥ፥ እንሽላሊት በየወገኑ፥ 30ኤሊ፥ አዞ፥ ገበሎ፥ አርጃኖ፥ እስስት። 31ከሚንቀሳቀሱት ሁሉ በእናንተ ዘንድ ርኩሳን የሚሆኑ እነዚህ ናቸው። ከእነርሱም በድናቸውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 32ከእነርሱም በድናቸው በምንም ላይ ቢወድቅ እርሱ ርኩስ ነው፤ የዕንጨት ዕቃ ወይም ልብስ ወይም ቍርበት ወይም ከረጢት ቢሆን የሚሠራበት ዕቃ ሁሉ እርሱን በውኃ ውስጥ ይንከሩት፤ እስከ ማታም ርኩስ ነው፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል። 33ከእነርሱም አንዳች በውስጡ የወደቀበትን የሸክላውን ዕቃ ሁሉ ስበሩት፤ በውስጡም ያለው ሁሉ ርኩስ ነው። 34በእርሱ ውስጥ ያለው፤ ውኃም የሚፈስስበት፥ የሚበላ መብል ሁሉ ርኩስ ነው፤ በዚህም ዕቃ ሁሉ ያለው የሚጠጣ መጠጥ ሁሉ ርኩስ ነው። 35ከእነዚህም በድን የሚወድቅበት ሁሉ ርኩስ ነው፤ እቶን ወይም ምድጃ ቢሆን ይሰባበራል፤ ርኩሳን ናቸውና፤ ለእናንተ ርኩሳን ይሆናሉ። 36ነገር ግን ምንጩ፥ ጉድጓዱም፥ የውኃውም ኵሬ ንጹሓን ናቸው፤ በድናቸውን ግን የሚነካ ርኩስ ነው። 37ከበድናቸውም በሚዘራ ዘር ላይ አንዳች ቢውድቅ እርሱ ንጹሕ ነው። 38ነገር ግን በዘሩ ላይ ውኃ ቢፈስስበት፥ ከዚህ በኋላ ከበድናቸው አንዳች ቢወድቅበት፥ ለእናንተ ርኩስ ነው።
39“ለመብል ከሚሆኑላችሁ እንስሳት የሞተ ቢኖር፥ በድኑን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 40ከበድኑም የሚበላ ልብሱን ያጥባል፤ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል፤ በድኑንም የሚያነሣ፤ ልብሱን ይጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው።
41“በምድርም ላይ የሚንቀሳቀስ ተንቀሳቃሽ አውሬ ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ነው፤ አትብሉትም። 42በሆዱ የሚሳብ፥ በአራትም እግሮች የሚሳብ፥ ብዙ እግሮችም ያሉት፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ ርኩሳን ናቸውና አትብሉአቸው። 43በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ ሰውነታችሁን አታርክሱ፤ በእነርሱም እንዳትረክሱ ሰውነታችሁን አታርክሱባቸው። 44እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና፤ ሰውነታችሁን ቀድሱ፤ ቅዱሳንም ሁኑ፤ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና፤ 45በምድርም ላይ በሚሳብ ተንቀሳቃሽ ሁሉ ሰውነታችሁን አታሳድፉ። እኔ አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ እንግዲህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።
46“የእንስሳና የወፍ፥ በውኃውም ውስጥ የሚንቀሳቀስ የፍጥረት ሁሉ፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀስ የፍጥረት ሁሉ ሕግ ይህ ነው። 47በርኩስና በንጹሕ መካከል፥ የሕይወት ነፍስ ካላቸውም በምትበሉትና በማትበሉት መካከል እንድትለዩ ነው።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 11: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ