መጽሐፈ ኢዮብ 32
32
1ኢዮብም በፊታቸው ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና እነዚያ ሦስቱ ወዳጆቹ ለኢዮብ ለመመለስ ዝም አሉ። 2ከአውስጢድ ሀገር ከአራም ወገን የሆነ የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ ኤሊዩስ ተቈጣ፥ በእግዚአብሔርም ፊት#ግሪክ ሰባ. ሊ. እና ዕብ. “ከእግዚአብሔር ይልቅ” ይላሉ። ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና ኢዮብን ተቈጣው። 3ደግሞም እንደ ኀጢአተኛ አደረጉት እንጂ ለኢዮብ የሚገባ መልስ መመለስ ስላልቻሉ በሦስቱ ባልንጀሮቹ ላይ ተቈጣ። 4ኤሊዩስ ግን ከእርሱ ይልቅ ሽማግሌዎች ነበሩና ለኢዮብ መልስ ለመስጠት ጠብቆ ነበር። 5ኤሊዩስም በእነዚህ በሦስቱ ሰዎች አፍ መልስ እንደሌለ ባየ ጊዜ በቍጣው ተቈጣቸው። 6የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ ኤልዩስም መለሰ፥ እንዲህም አለ፥ “እኔ በዕድሜዬ ታናሽ ነኝ፥ እናንተ ግን ሽማግሌዎች ናችሁ፤ ስለዚህም ዕውቀቴን እገልጥላችሁ ዘንድ ፈርቼ ዝም አልሁ።
7እንደዚህም አልሁ፥ “የሚናገሩ ዓመታት አይደሉም፥
በዓመታት ብዛት ሰዎች ጥበብን አያውቋትም።
8ነገር ግን በሟች ሰው ውስጥ መንፈስ አለ፥
ሁሉን የሚችል የእግዚአብሔር መንፈስም ያስተምራል።
9በዕድሜ ያረጁ ጠቢባን አይደሉም፥
ሽማግሌዎችም ፍርድን አያስተውሉም።
10ነገር ግን፦ ስሙኝ፤
እኔ ደግሞ የማውቀውን እገልጥላችኋለሁ አልሁ።
11እነሆ፥ ንግግሬን አድምጡኝ፤
የምትናገሩትን ነገር እስክትመረምሩ ድረስ
እየሰማችሁት እነግራችኋለሁ።
12እንዲሁም ልብ አደረግሁ፤
እነሆም፥ ከእናንተ መካከል ኢዮብን የገሠጸ፥
ወይም ለተናገረው ቃልን የመለሰ የለም።
13እናንተም፦ ከእግዚአብሔር ጥበብን አግኝተናል፤
አብዝተናልም እንዳትሉ ተጠንቀቁ።
14እናንተ ግን እንዲህ ያለ ነገር እንዲናገር
ለሰው መብት ሰጣችሁት።
15“እናንተ ፈራችሁ፥ ዳግመኛም አልመለሳችሁም፤
ከአፋችሁም ቁም ነገር ጠፋ።
16እኔ በትዕግሥት ጠበቅሁ እንጂ አልተናገርሁም።
እናንተ ዝም ብላችሁ ቆማችሁ፥ አልመለሳችሁምና።”#ግሪክ ሰባ. ሊ. በሦስተኛ መደብ ይጽፋል።
17ኤልዩስም መለሰ፥ እንዲህም አለ፦
“ደግሜ እናገራለሁ።
18እኔ ቃል ተሞልቻለሁና፥
በውስጤም ያለ መንፈስ አስጨንቆኛልና።
19በተሃ ጠጅ እንደ ተሞላና ሊቀደድ እንደ ቀረበ አቁማዳ፥
ወይም እንደ አንጥረኛ ወናፍ እነሆ፥ አንጀቴ ሆነ።
20ጥቂት እንድተነፍስ እናገራለሁ።
ከንፈሬንም ገልጬ እመልሳለሁ።
21ከሰው የተነሣ አላፍርምና፥
ከሟች ሰውም የተነሣ አላፈገፍግምና።
22ለሰው ፊት ማድላትን አላውቅም፤
ከሰውም የተነሣ የማፍረው ካለ ትሎች ይብሉኝ።#ምዕ. 32 ቍ. 22 ከዕብራይስጡ ልዩነት አለው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 32: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ