ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ የእግዚአብሔር መላእክት መጥተው በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ፥ ሰይጣን ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም ከእነርሱ ጋር መጣ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፥ “ከወዴት መጣህ?” አለው። ሰይጣንም፥ “ከሰማይ በታች በምድር ላይ ዞርሁ፥ በእርስዋም ተመላለስሁ” ብሎ በእግዚአብሔር ፊት መለሰ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን አለው፥ “በባሪያዬ በኢዮብ ላይ እንዲህ እንዳታስብ ተጠንቀቅ፤ በምድር ላይ እንደ እርሱ ያለ ገር፥ ጻድቅና ንጹሕ፥ እግዚአብሔርን የሚፈራ፥ ከክፋትም ሁሉ የራቀ፥ ዳግመኛም ቅን የሆነ ሰው የለምና፤ አንተ ግን ሀብቱን በከንቱ አጠፋ ዘንድ ነገርኸኝ።” ሰይጣንም መልሶ ለእግዚአብሔር፥ “ቍርበት ስለ ቍርበት ነው፤ ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል። ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ አጥንቱንና ሥጋውን ዳስስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል” ብሎ መለሰ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን አለው፥ “እነሆ፥ ሥጋውንና አጥንቱን በእጅህ ሰጠሁህ። ነገር ግን ሕይወቱን ተው።” ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፥ ኢዮብንም ከእግሩ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቍስል መታው። ቍስሉንም ያክክበት ዘንድ ገል ወሰደ፥ ከከተማም ወጥቶ በአመድ ላይ ተቀመጠ። ብዙ ወራትም ካለፈ በኋላ ሚስቱ እንዲህ አለችው፥ “እስከ መቼ ትታገሣለህ? 9 ‘ሀ’ ዳግመኛም እግዚአብሔርን ጥቂት ወራት ደጅ እጠናዋለሁ፤ ዳግመኛም መከራውን እታገሠዋለሁ፤ የቀድሞው ኑሬዬንም ተስፋ አደርገዋለሁ ትላለህን? 9 ‘ለ’ እንደዚህስ እንዳትል ከዚህ ዓለም እነሆ ስም አጠራርህ ጠፋ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቼም ሞቱ፥ ማኅፀኔም በምጥ ተጨነቀ፥ በከንቱም ደከምሁ። 9 ‘ሐ’ አንተም በመግልና በትል ትኖራለህ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ትዛብራለህ። 9 ‘መ’ እኔ ግን እየዞርሁ እቀላውጣለሁ። ከአንዱ መንደር ወደ አንዱ መንደር፥ ከአንዱ ቤትም ወደ አንዱ ቤት እሄዳለሁ፤ ከድካሜና በእኔ ላይ ካለ ችግሬም ዐርፍ ዘንድ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ እጠብቃለሁ፤ ነገር ግን አሁን እግዚአብሔርን ስደብና ሙት።” እርሱ ግን፦ ወደ እርስዋ ተመለከተና እንዲህ አላት፥ “አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፤ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉውን ነገርስ አንታገሥምን?” በዚህ በደረሰበት ሁሉ ኢዮብ በእግዚአብሔር ፊት በከንፈሩ አልበደለም። ሦስቱም የኢዮብ ወዳጆች ይህን የደረሰበትን ክፉ ነገር ሁሉ ሰምተው ከየሀገራቸው ወደ እርሱ መጡ፤ እነርሱም ቴማናዊው ንጉሥ ኤልፋዝ፥ አውኬናዊው መስፍን በልዳዶስ፥ አሜናዊው ንጉሥ ሶፋር ነበሩ። እነርሱም ሊጐበኙትና ሊያጽናኑት በአንድነት ወደ እርሱ መጡ። ከሩቅም ሆነው ባዩት ጊዜ አላወቁትም፤ በታላቅ ድምፅም ጮኸው አለቀሱ፤ መጐናጸፊያቸውንም ቀደዱ፥ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊትም በአጠገቡ ተቀመጡ፤ ሕማሙ እጅግ አስፈሪና ታላቅ እንደ ነበረ አይተዋልና ከእነርሱ አንድ ቃል የሚናገረው አልነበረም።
መጽሐፈ ኢዮብ 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢዮብ 2:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች