የዮ​ሐ​ንስ ወን​ጌል 6:22-44

የዮ​ሐ​ንስ ወን​ጌል 6:22-44 አማ2000

በማ​ግ​ሥ​ቱም ከባ​ሕሩ ዳር ቆመው የነ​በሩ ሰዎች ከአ​ን​ዲት ታንኳ በቀር ከዚያ ሌላ ታንኳ እን​ዳ​ል​ነ​በረ፥ ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም ለብ​ቻ​ቸው ሄዱ እንጂ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ከደቀ መዛ​ሙ​ርቱ ጋር ወደ ታንኳ እን​ዳ​ል​ወጣ አዩ። ደግ​ሞም ጌታ​ችን የባ​ረ​ከ​ውን እን​ጀራ ከበ​ሉ​በት ቦታ አቅ​ራ​ቢያ ከጥ​ብ​ር​ያ​ዶስ ሌሎች ታን​ኳ​ዎች መጥ​ተው ነበር። እነ​ዚያ ሰዎ​ችም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ፥ ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም በዚያ እን​ዳ​ል​ነ​በሩ ባዩ ጊዜ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስን ይፈ​ል​ጉት ዘንድ በእ​ነ​ዚያ ታን​ኳ​ዎች ገብ​ተው ወደ ቅፍ​ር​ና​ሆም መጡ። በባ​ሕሩ ዳርም ባገ​ኙት ጊዜ፥ “መም​ህር ሆይ፥ ወደ​ዚህ መቼ መጣህ?” አሉት። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እው​ነት እው​ነት እላ​ች​ኋ​ለሁ፤ እና​ንተ የም​ት​ፈ​ል​ጉኝ እን​ጀራ ስለ በላ​ች​ሁና ስለ ጠገ​ባ​ችሁ ነው እንጂ ተአ​ም​ራት ስለ አያ​ችሁ አይ​ደ​ለም። የሰው ልጅ ለሚ​ሰ​ጣ​ችሁ ለዘ​ለ​ዓ​ለም ሕይ​ወት ለሚ​ኖር መብል ሥሩ እንጂ ለሚ​ጠ​ፋው መብል አይ​ደ​ለም፤ ይህን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አብ አት​ሞ​ታ​ልና።” “እን​ግ​ዲህ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ሥራ እን​ሠራ ዘንድ ምን እና​ድ​ርግ?” አሉት። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ፥ “ይህ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሥራ እርሱ በላ​ከው ታምኑ ዘንድ ነው፤” አላ​ቸው። እነ​ር​ሱም እን​ዲህ አሉት፥ “የም​ት​ሠ​ራ​ውን አይ​ተን በአ​ንተ እና​ምን ዘንድ ምን ተአ​ም​ራት ታደ​ር​ጋ​ለህ? አባ​ቶ​ቻ​ች​ንስ ‘ሊበሉ እን​ጀራ ከሰ​ማይ ሰጣ​ቸው’ ተብሎ እንደ ተጻፈ በም​ድረ በዳ መና በሉ። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እው​ነት እው​ነት እላ​ች​ኋ​ለሁ፤ ያን እን​ጀራ ከሰ​ማይ የሰ​ጣ​ችሁ ሙሴ አይ​ደ​ለም፤ አባቴ ከሰ​ማይ የእ​ው​ነት እን​ጀ​ራን ሰጥ​ቶ​አ​ች​ኋል እንጂ። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ጀራ ከሰ​ማይ የሚ​ወ​ርድ፤ ለዓ​ለ​ምም ሕይ​ወ​ትን የሚ​ሰጥ ነውና።” እነ​ር​ሱም፥ “አቤቱ ከዚያ እን​ጀራ ሁል​ጊዜ ስጠን” አሉት። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “የሕ​ይ​ወት እን​ጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚ​መጣ ከቶ አይ​ራ​ብም፤ በእኔ የሚ​ያ​ም​ንም ለዘ​ለ​ዓ​ለም አይ​ጠ​ማም። ነገር ግን እላ​ች​ኋ​ለሁ፤ አያ​ች​ሁኝ፤ አላ​መ​ና​ች​ሁ​ብ​ኝ​ምም። አብ የሚ​ሰ​ጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመ​ጣል፤ ወደ እኔ የሚ​መ​ጣ​ው​ንም ከቶ ወደ ውጭ አላ​ወ​ጣ​ውም። ከሰ​ማይ የወ​ረ​ድሁ የላ​ከ​ኝን ፈቃድ እንጂ፥ ፈቃ​ዴን ላደ​ርግ አይ​ደ​ለ​ምና። የላ​ከኝ የአብ ፈቃ​ድም ይህ ነው፤ ከሰ​ጠኝ ሁሉ አን​ድስ እንኳ ቢሆን እን​ዳ​ይ​ጠፋ ነው፤ ነገር ግን እኔ በኋ​ለ​ኛ​ዪቱ ቀን አስ​ነ​ሣ​ዋ​ለሁ። የአ​ባቴ ፈቃዱ ይህ ነው፤ ወል​ድን አይቶ የሚ​ያ​ም​ን​በት ሁሉ የዘ​ለ​ዓ​ለም ሕይ​ወ​ትን እን​ዲ​ያ​ገኝ ነው፤ እኔም በመ​ጨ​ረ​ሻ​ዪቱ ቀን አስ​ነ​ሣ​ዋ​ለሁ።” አይ​ሁ​ድም ስለ እርሱ አን​ጐ​ራ​ጐሩ፤ “ከሰ​ማይ የወ​ረደ የሕ​ይ​ወት እን​ጀራ እኔ ነኝ” ብሎ​አ​ቸ​ዋ​ልና። “እኛ አባ​ቱ​ንና እና​ቱን የም​ና​ው​ቃ​ቸው ይህ የዮ​ሴፍ ልጅ ኢየ​ሱስ አይ​ደ​ለ​ምን? እን​ግ​ዲህ እን​ዴት ከሰ​ማይ ወረ​ድሁ ይለ​ናል?” አሉ። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እርስ በር​ሳ​ችሁ አታ​ን​ጐ​ራ​ጕሩ። የላ​ከኝ አብ ካል​ሳ​በው በቀር ወደ እኔ መም​ጣ​ትን የሚ​ችል የለም፤ እኔም በመ​ጨ​ረ​ሻ​ዪቱ ቀን አስ​ነ​ሣ​ዋ​ለሁ።