በማግስቱም በባሕሩ ማዶ የቀሩት ሰዎች በዚያ አንዲት ጀልባ ብቻ እንደ ነበረች ተረዱ፤ ኢየሱስ እንዳልተሳፈረና ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን እንደ ሄዱም ዐወቁ። ከዚያም በኋላ፣ ሌሎች ጀልባዎች ከጥብርያዶስ ሕዝቡ ጌታ የባረከውን እንጀራ ወደ በላበት ስፍራ መጡ። ሰዎቹም፣ ኢየሱስ ወይም ደቀ መዛሙርቱ በዚያ አለመኖራቸውን እንዳወቁ፣ ኢየሱስን ፍለጋ በጀልባዎቹ ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ። ከባሕሩ ማዶ ባገኙትም ጊዜ፣ “ረቢ፤ መቼ ወደዚህ መጣህ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ እንጂ፣ ታምራዊ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም። ለሚጠፋ እንጀራ አትሥሩ፤ ነገር ግን የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር ምግብ ሥሩ፤ ለዚህም እግዚአብሔር አብ ማረጋገጫ ማኅተሙን በርሱ ላይ ዐትሟልና።” እነርሱም፣ “ታዲያ የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን ማድረግ አለብን?” አሉት። ኢየሱስም፣ “እርሱ በላከው ታምኑ ዘንድ፣ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነው” ሲል መለሰላቸው። ስለዚህ እንዲህ ብለው ጠየቁት፤ “አይተን እንድናምንህ ምን ታምራዊ ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? ‘ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራን ሰጣቸው’ ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ።” ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ እውነተኛውን እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ ግን አባቴ ነው፤ የእግዚአብሔር እንጀራ፣ እርሱ ከሰማይ የሚወርድ፣ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና።” እነርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ እንግዲያውስ ይህን እንጀራ ሁልጊዜ ስጠን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔም የሚያምን ፈጽሞ አይጠማም። ነገር ግን እንደ ነገርኋችሁ፣ አይታችሁኝም እንኳ አታምኑም። አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤ ከሰማይ የወረድሁት የራሴን ፈቃድ ለማድረግ ሳይሆን፣ የላከኝን የርሱን ፈቃድ ለመፈጸም ነውና፤ የላከኝም ፈቃድ፣ ከሰጠኝ ሁሉ አንድ እንኳ ሳይጠፋብኝ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣ ነው። የአባቴ ፈቃድ ወልድን አይቶ በርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።” አይሁድም፣ “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ” በማለቱ ያጕረመርሙበት ጀመር። ደግሞም፣ “ይህ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው፣ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? ታዲያ አሁን እንዴት፣ ‘ከሰማይ ወረድሁ ይላል’ ” አሉ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በርሳችሁ አታጕረምርሙ፤ የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ማንም ወደ እኔ መምጣት አይችልም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።
ዮሐንስ 6 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 6
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 6:22-44
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች