ጲላጦስም ጽሕፈት ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረ፤ ጽሕፈቱም፥ “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ነበር። ከአይሁድም ይህቺን ጽሕፈት ያነበብዋት ብዙዎች ነበሩ፤ ጌታችን ኢየሱስን የሰቀሉበት ቦታ ለከተማ ቅርብ ነበርና፤ ጽሕፈቱም የተጻፈው በዕብራይስጥ፥ በሮማይስጥና በግሪክ ነበር። ሊቃነ ካህናትም ጲላጦስን አሉት፥ “እርሱ ራሱ ‘እኔ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ’ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትጻፍ።” ጲላጦስም፥ “የጻፍሁትን ጻፍሁ” ብሎ መለሰላቸው። ጭፍሮችም ጌታችን ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ከጭፍሮቹ ለእያንዳንዱ አራት ክፍል አድርገው መደቡት፤ ቀሚሱንም ወሰዱ፤ ቀሚሱም ከላይ ጀምሮ የተሠራ ሥረወጥ እንጂ የተሰፋ አልነበረም። እርስ በርሳቸውም፥ “ዕጣ እንጣጣልና ለደረሰ ይድረሰው እንጂ አንቅደደው ተባባሉ፤” ይህም “ልብሶችን ለራሳቸው ተካፈሉ፤ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” ያለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው፤ ጭፍሮችም እንዲሁ አደረጉ። በጌታችን በኢየሱስ መስቀል አጠገብም እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊት ማርያምም ቆመው ነበር። ጌታችን ኢየሱስም እናቱንና የሚወደውን ደቀ መዝሙሩን ቆመው ባያቸው ጊዜ እናቱን፥ “አንች ሆይ፥ እነሆ፥ ልጅሽ” አላት። ከዚህም በኋላ ደቀ መዝሙሩን፥ “እናትህ እነኋት” አለው፤ ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ተቀብሎ ወደ ቤቱ ወሰዳት። ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ሁሉ እንደ ተፈጸመ ባየ ጊዜ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ “ተጠማሁ” አለ። በዚያም ሆምጣጤ የመላበት ማሰሮ ነበር፤ እነርሱም ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው በስምዛ ዘንግ ከአፉ አገናኝተው ጨመቁት። ጌታችን ኢየሱስም ሆምጣጤውን ቀምሶ፥ “ሁሉ ተፈጸመ” አለ፤ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን ሰጠ። አይሁድ ግን የመዘጋጀት ቀን ነበርና፥ የዚያች ሰንበትም ቀን ታላቅ ናትና “ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ አይደር” አሉ፤ ጭን ጭናቸውንም ሰብረው ያወርዷቸው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት። ጭፍሮችም መጥተው ከእርሱ ጋር የተሰቀሉትን የአንደኛውንና የሁለተኛውን ጭኖች ሰበሩ። ወደ ጌታችን ኢየሱስም ሄደው ፈጽሞ እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ ጭኑን አልሰበሩም። ነገር ግን ከጭፍሮቹ አንዱ የቀኝ ጎኑን በጦር ወጋው፤ ያንጊዜም ከእርሱ ደምና ውኃ ወጣ። ያየውም መሰከረ፤ ምስክርነቱም እውነት ነው፤ እርሱም እናንተ ልታምኑ እውነት እንደሚናገር ያውቃል። ይህ ሁሉ የሆነው “ከእርሱ ዐፅሙን አትስበሩ” ያለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ሌላዉም መጽሐፍ ደግሞ“ የወጉትን ያዩታል” ይላል። ከዚህም በኋላ አይሁድን ስለፈራ በስውር የጌታችን የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረው የአርማትያስ ሰው ዮሴፍ የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ይወስድ ዘንድ ጲላጦስን ለመነው፤ ጲላጦስም ፈቀደለት። እርሱም ሄዶ የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ወሰደ። ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሄዶ የነበረው ኒቆዲሞስም መጣ፤ ቀብተውም የሚቀብሩበትን መቶ ወቄት የከርቤና የሬት ቅልቅል ሽቶ አመጣ። እንደ አይሁድ አገናነዝ ሥርዐትም የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ወስደው ከሽቱ ጋር በበፍታ ገነዙት። በዚያም በተሰቀለበት ቦታ የአትክልት ስፍራ ነበር፤ በዚያ የአትክልት ስፍራ ውስጥም በውስጡ ሰው ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር። ጌታችን ኢየሱስንም በዚያ ቀበሩት፤ ለአይሁድ የመሰናዳት ቀን ነበርና፤ መቃብሩም ለሰቀሉበት ቦታ ቅርብ ነበር።
የዮሐንስ ወንጌል 19 ያንብቡ
ያዳምጡ የዮሐንስ ወንጌል 19
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 19:19-42
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች