ዮሐንስ 19:19-42

ዮሐንስ 19:19-42 NASV

ጲላጦስም ጽሑፍ ጽፎ በመስቀሉ ላይ አንጠለጠለው፤ ጽሑፉም፣ “የናዝሬቱ ኢየሱስ፣ የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ነበር። ኢየሱስ የተሰቀለበት ቦታ ከከተማው አጠገብ ስለ ነበር ብዙዎቹ አይሁድ ጽሑፉን አነበቡት፤ ጽሑፉም፣ በአራማይክና በላቲን፣ በግሪክም ነበር። የአይሁድ የካህናት አለቆች ጲላጦስን በመቃወም፣ “እርሱ፣ ‘የአይሁድ ንጉሥ ነኝ’ እንዳለ ጻፍ እንጂ ‘የአይሁድ ንጉሥ’ ብለህ አትጻፍ” አሉት። ጲላጦስም፣ “በቃ፤ የጻፍሁትን ጽፌአለሁ” ብሎ መለሰ። ወታደሮቹ ኢየሱስን ከሰቀሉ በኋላ፣ እጀ ጠባቡ ሲቀር፣ ልብሱን ወስደው ለእያንዳንዱ አንድ አንድ እንዲዳረስ ለአራት ተከፋፈሉት፤ እጀ ጠባቡም ከላይ እስከ ታች አንድ ወጥ ሆኖ ያለ ስፌት የተሠራ ነበር። ስለዚህ፣ “ዕጣ ተጣጥለን ለሚደርሰው ይድረስ እንጂ አንቅደደው” ተባባሉ። ይህም የሆነው፣ “ልብሴን ተከፋፈሉት፤ በእጀ ጠባቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው። ወታደሮቹ ያደረጉትም ይህንኑ ነው። በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱና የእናቱ እኅት፣ እንዲሁም የቀለዮጳ ሚስት ማርያምና መግደላዊት ማርያም ቆመው ነበር። በዚያም ኢየሱስ እናቱንና የሚወድደውም ደቀ መዝሙር አጠገቧ ቆሞ ሲያያቸው እናቱን፣ “አንቺ ሴት ሆይ፤ ልጅሽ ይኸው” አላት፤ ደቀ መዝሙሩንም፣ “እናትህ ይህችው” አለው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይህ ደቀ መዝሙር ወደ ቤቱ ወሰዳት። ከዚያም ኢየሱስ ሁሉ ነገር እንደ ተፈጸመ ዐውቆ፣ የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም፣ “ተጠማሁ” አለ። በዚያም የኮመጠጠ ወይን የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሰፍነግ በወይን ጠጅ ነክረው፣ በሂሶጵ ዘንግ ወደ አፉ አቀረቡለት፤ ኢየሱስም ኮምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ፣ “ተፈጸመ” አለ፤ ራሱን አዘንብሎ፣ መንፈሱን አሳልፎ ሰጠ። ዕለቱ ለሰንበት መዘጋጃ ቀን ነበር። አይሁድ፣ የተሰቀሉት ሰዎች ሬሳ በሰንበት ቀን በመስቀል ላይ እንዳይውል ስለ ፈለጉና ያም የተለየ ሰንበት ስለ ነበር፣ የተሰቀሉት ሰዎች ጭናቸው ተሰብሮ በድናቸው እንዲወርድ ጲላጦስን ለመኑት። ስለዚህም ወታደሮቹ መጥተው ከክርስቶስ ጋራ ተሰቅሎ የነበረውን የመጀመሪያውን ሰው ጭን ሰበሩ፤ ደግሞም የሌላውን ጭን ሰበሩ። ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን ሞቶ ስላገኙት ጭኖቹን አልሰበሩም፤ ነገር ግን ከወታደሮቹ አንዱ የኢየሱስን ጐን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውሃ ፈሰሰ። ይህን ያየው ሰው ምስክርነቱን ሰጥቷል፤ ምስክርነቱም እውነት ነው፤ እውነትን እንደሚናገርም ያውቃል፤ እናንተም እንድታምኑ ይመሰክራል። ይህም የሆነው፣ መጽሐፍ፣ “ከዐጥንቱ አንድም አይሰበርም” ያለው እንዲፈጸም፣ ሌላውም መጽሐፍ፣ “የወጉትም ያዩታል” ስለሚል ነው። ከዚህ በኋላ የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስን በድን ለመውሰድ ጲላጦስን ለመነው፤ ዮሴፍም አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር። እርሱም ጲላጦስን ካስፈቀደ በኋላ መጥቶ በድኑን ወሰደ። ከዚህ ቀደም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስ አንድ መቶ ሊትር ያህል የሚመዝን የከርቤና የአደስ ቅልቅል ይዞ መጣ። እነርሱም የኢየሱስን በድን ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋራ ከተልባ እግር በተሠራ ጨርቅ ከፈኑት። ኢየሱስ በተሰቀለበት ቦታም የአትክልት ስፍራ ነበር፤ በአትክልቱም ስፍራ ማንም ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር። ዕለቱ ለአይሁድ የሰንበት መዘጋጃ ቀን ስለ ነበርና መቃብሩም ቅርብ ስለ ነበር ኢየሱስን በዚያ ቀበሩት።