የዮሐንስ ወንጌል 1
1
ስለ ቃል ቀዳማዊነት
1በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። 2ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። 3ሁሉም በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም። 4ሕይወት በእርሱ ነበረ፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፤ 5ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም አላገኘውም።
ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መላክ
6 #
ማቴ. 3፥1፤ ማር. 1፥4፤ ሉቃ. 3፥1-2። ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበር። 7እርሱም ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምን ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክርነት መጣ። 8ስለ ብርሃን ምስክር ሊሆን መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም።
9ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃንስ ወደ ዓለም የመጣው ነው። 10በዓለም ነበረ፤ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፤ ዓለሙ ግን አላወቀውም። 11ወደ ወገኖቹ መጣ፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። 12ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው። 13እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር ወይም ከወንድና ከሴት#“ከሴት” የሚለው በግሪኩ እኛ በአብዛኛው የግእዝ ዘርዕ የለም። ፈቃድ አልተወለዱም።
ቃል ሥጋ ስለመሆኑ
14ያም ቃል ሥጋ ሆነ፤ በእኛም አደረ፤ ለአባቱ አንድ እንደ ሆነ ልጅ ክብር ያለ ክብሩን አየን፤ ጸጋንና እውነትን የተመላ ነው። 15ምስክሩ ዮሐንስ ስለ እርሱ ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ፤ እንዲህም አለ፥ “እኔ ስለ እርሱ ከእኔ በፊት የነበረ ከእኔ በኋላ ይመጣል ያልኋችሁ ሰው ይህ ነው፥ እርሱ ከእኔ አስቀድሞ ነበረና።” 16እኛም ሁላችን ከሙላቱ በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀበልን። 17ኦሪት በሙሴ ተሰጥታን ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነልን። 18በአባቱ ዕቅፍ ያለ አንድ ልጅ እርሱ ገለጠልን እንጂ እግዚአብሔርንስ ከቶ ያየው የለም።
ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት
19አይሁድ፥ “አንተ ማን ነህ?” ብለው ይጠይቁት ዘንድ ካህናትንና ሌዋውያንን ከኢየሩሳሌም በላኩ ጊዜ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው። 20እርሱም፥ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም” ብሎ አመነ እንጂ አልካደም። 21#ዘዳ. 18፥15፤ 18፤ ሚል. 4፥5። “እንኪያ አንተ ማነህ? አንተ ኤልያስ ነህን?” ብለው ጠየቁት፤ “አይደለሁም” አለ፤ “እንኪያ አንተ ነቢዩ ነህን?” አሉት፤ “አይደለሁም” አለ። 22“እንኪያስ አንተ ማነህ? ለላኩንም መልስ እንድንሰጥ ስለ ራስህ ማን ትላለህ?” አሉት። 23#ኢሳ. 40፥3። እርሱም፥ “ነቢዩ ኢሳይያስ እንደ ተናገረ የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ እያለ በምድረ በዳ የሚሰብክ የዐዋጅ ነጋሪ ድምፅ እኔ ነኝ” አለ። 24የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩ። 25“እንኪያስ ክርስቶስን ካልሆንህ፥ ኤልያስንም ካልሆንህ፥ ነቢይንም ካልሆንህ ለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት። 26ዮሐንስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እኔ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤#በግሪኩ “አጠምቃለሁ” ይላል። ነገር ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል። 27ከእኔ በኋላ የሚመጣው፥ ከእኔ በፊት የነበረው፥ የጫማውን ጠፍር ልፈታ እንኳ የማይገባኝ ነው።”#“እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል” የሚል በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ ይገኛል። 28ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ እንዲህ ሆነ።
29በማግሥቱም ዮሐንስ ወደ እርሱ ሲመጣ ጌታችን ኢየሱስን አይቶ እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ የዓለሙን ኀጢኣት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። 30ከእኔ በፊት የነበረ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል ብዬ ስለ እርሱ የነገርኋችሁ ይህ ነው፤ እርሱ ከእኔ አስቀድሞ ነበርና። 31እኔ አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን እስራኤል እንዲያውቁት ስለዚህ እኔ በውኃ ላጠምቅ መጣሁ።” 32ዮሐንስም ምስክርነቱን እንዲህ ብሎ ተናገረ፥ “መንፈስ ቅዱስ ከሰማይ እንደ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየሁ። 33እኔም አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን በውኃ እንዳጠምቅ የላከኝ እርሱ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ሲቀመጥበት የምታየው በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። 34እኔም ራሴ አይቻለሁ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እኔ ምስክሩ ነኝ።”
ስለ መጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት
35በማግሥቱም ደግሞ ዮሐንስ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ቆሞ ሳለ፥ 36ጌታችን ኢየሱስን ሲሄድ አይቶ “እነሆ፥ የዓለሙን ኀጢኣት የሚያስወግድ#“የዓለሙን ኀጢኣት የሚያሰወግድ ...” የሚለው በግሪኩ የለም። የእግዚአብሔር በግ” አለ። 37ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ ሲል ሰምተው ጌታችን ኢየሱስን ተከተሉት። 38ጌታችን ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉት አየና፥ “ምን ትሻላችሁ?” አላቸው። 39እነርሱም፥ “ረቢ፥ ትርጓሜውም መምህር ሆይ፥ ማለት ነው፤ ወዴት ትኖራለህ?” አሉት። 40እርሱም “መጥታችሁ እዩ” አላቸው፤ ሄደውም የሚኖርበትን አዩ፤ ያን ዕለትም እስከ ዐሥር ሰዓት ድረስ በእርሱ ዘንድ ዋሉ። 41ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ጌታችን ኢየሱስን ከተከተሉት ከሁለቱም አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበር። 42እርሱም መጀመሪያ ወንድሙ ስምዖንን አግኝቶ “በትርጓሜው ክርስቶስ የሚሉት መሲሕን አገኘነው” አለው። 43እርሱም ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ወሰደው፤ ጌታችን ኢየሱስም ባየው ጊዜ፥ “ አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህን? አንተ ኬፋ ትባላለህ፤” አለው፤ ትርጓሜውም ጴጥሮስ ማለት ነው።
ስለ ፊልጶስና ስለ ናትናኤል
44በማግሥቱም ጌታችን ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊሄድ ወደደ፤ ፊልጶስንም አገኘውና “ተከተለኝ” አለው። 45ፊልጶስ ግን ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበር። 46ፊልጶስም ናትናኤልን አገኘውና፥ “ሙሴ በኦሪት፥ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው” አለው። 47ናትናኤልም፥ “በውኑ ከናዝሬት ደግ ሰው#በግሪኩ “መልካም ነገር” ይላል። ሊወጣ ይቻላልን?” አለው፤ ፊልጶስም፥ “መጥተህ እይ” አለው። 48ጌታችን ኢየሱስም ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ ባየው ጊዜ ስለ እርሱ “እነሆ፥ በልቡ ተንኰል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ ይህ ነው” አለ። 49ናትናኤልም፥ “በየት ታውቀኛለህ?” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ገና ፊልጶስ ሳይጠራህ በበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ አይችሃለሁ” አለው። 50ናትናኤልም መልሶ፥ “መምህር ሆይ፥ በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ የእስራኤልም ንጉሥ አንተ ነህ” አለው። 51#ዘፍ. 28፥12። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “በበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ ስለ አልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ታያለህ” አለው። 52“እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰማያት ሲከፈቱ፥ የእግዚአብሔርም መላእክት ወደ ሰው ልጅ ሲወርዱና ሲወጡ ታያላችሁ” አላቸው።
Currently Selected:
የዮሐንስ ወንጌል 1: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ