ትንቢተ ኤርምያስ 8
8
1“በዚያም ዘመን ይላል እግዚአብሔር፤ የይሁዳ ነገሥታትን አጥንትና የመኳንንቱን አጥንት፥ የካህናቱን አጥንትና የነቢያቱን አጥንት፥ የኢየሩሳሌምንም ሰዎች አጥንት ከመቃብሮቻቸው ያወጣሉ። 2በወደዱአቸውና በአመለኳቸው፥ በተከተሉአቸውና በፈለጓቸው፥ በሰገዱላቸውም በፀሐይና በጨረቃ፥ በከዋክብትም፥ በሰማይም ሠራዊት ሁሉ ፊት ይዘረጓቸዋል፤ አያለቅሱላቸውም፤ አይቀብሯቸውምም፤ በምድርም ፊት ላይ እንደ ጕድፍ ይሆናሉ። 3እኔም ባሳደድኋቸው ስፍራ ሁሉ የቀሩ፥ ከዚህች ክፉ ትውልድ የተረፉ ቅሬቶች ሁሉ፥ ከሕይወት ይልቅ ሞትን ይመርጣሉ።”
4እንዲህም ትላቸዋለህ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የወደቀ አይነሣምን? የሳተስ አይመለስምን? 5ሕዝቤ በኢየሩሳሌም#“ሕዝቤ በኢየሩሳሌም” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ስለ ምን ወደ ኋላቸው ተመለሱ? ዐመፅን ዐምፀዋል፥ መመለስንም እንቢ ብለዋል። 6አደመጥሁ፤ ሰማሁም፤ ቅንን ነገር አልተናገሩም፤ ማናቸውም፦ ምን አድርጌአለሁ? ብሎ ከክፋቱ ንስሓ የገባ የለም፤ የሚሮጠውም ወደ ሰልፍ እንደሚሮጥ ፈረስ ሲሮጥ ደከመ። 7ሽመላ በሰማይ ጊዜዋን አውቃለች፤ ዋኖስና ጨረባ፥ ዋሊያም የመምጣታቸውን ጊዜ ይጠብቃሉ፤ ሕዝቤ ግን የእግዚአብሔርን ፍርድ አላወቁም።
8“እናንተስ፦ ጥበበኞች ነን የእግዚአብሔርም ሕግ ከእኛ ጋር ነው እንዴት ትላላችሁ? እነሆ ጸሓፊዎቻቸውም ከንቱ ሆኑ፤ በሐሰትም ብርዕ ተጠቀሙ።#ዕብ. “የጸሓፊ ብርዕ ሐሰተኛ ነው ፤ በሐሰትም አድርጎአል” ይላል። 9ጥበበኞች አፍረዋል፤ ደንግጠውማል፤ ተማርከውማል፤ እነሆ የእግዚአብሔርን ቃል ጥለዋል፤ ምን ዓይነት ጥበብ አላቸው? 10ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ስስትን ያስባሉና፥ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉ በተንኰል ያደርጋሉና#“ሁሉ ስስትን ያስባሉና፥ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉ በተንኰል ያደርጋሉና” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ስለዚህ ሚስቶቻቸውን ለሌሎች፥ እርሻቸውንም ለሚወርሱባቸው እሰጣለሁ። 11የሕዝቤንም ሴት ልጅ ስብራት በማቃለል ይፈውሳሉ፤ ሰላም ሳይሆን፦ ሰላም ሰላም ይላሉ። 12አስጸያፊ ነገርን ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፤ እፍረትንም አላወቁም፤ ስለዚህ ከሚወድቁ ጋር ይወድቃሉ፤ በጐበኘኋቸውም ጊዜ ይዋረዳሉ፤ ይላል እግዚአብሔር። 13አዝመራቸውን ይሰበስባሉ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን በወይን ላይ ፍሬ፥ በበለስ ዛፍ ላይ በለስ የለም፤ ቅጠልም ይረግፋል፤ ሰጠኋቸው፤ አለፈባቸውም።
14“ዝም ብለን ለምን እንቀመጣለን? እግዚአብሔርን ስለ በደልን አምላካችን እግዚአብሔር አጥፍቶናልና፥ የሐሞትንም ውኃ አጠጥቶናልና ተሰብስባችሁ ወደ ተመሸጉ ከተሞች እንግባ በዚያም እንጥፋ። 15ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፤ ለይቅርታም ጊዜ መልካም ነገርን አጣን፤ እነሆም ድንጋጤ ሆነ። 16የፈረሶቹን የሩጫ ድምፅ ከዳን ሰማን፤ ከሠራዊቱ ፈረሶች ሩጫ ድምፅ የተነሣም ምድር በመላዋ ተንቀጠቀጠች፤ መጥተውም ምድሪቱንና በእርስዋም ያለውን ሁሉ፥ ከተማዪቱንና የተቀመጡባትንም በሉ። 17እነሆ አስማት የማይከለክላቸውን የሚገድሉ እባቦችን እሰድድባችኋለሁ፤ እነርሱም ይነድፉአችኋል፥” ይላል እግዚአብሔር።
18ልባችሁን ታምማችሁ ትቅበዘበዛላችሁ። ከሚያቅበዘብዝ የልብ ሕመማችሁ የሚያድናችሁ የለም።#ዕብ. “ኀዘኔ የማይጽናና ነው ፤ ልቤም በውስጤ ደክሞአል” ይላል። 19እነሆ እግዚአብሔር በጽዮን የለምን? ወይስ ንጉሥዋ በእርስዋ ዘንድ የለምን? የሚል የወገኔ ሴት ልጅ ጩኸት ድምፅ ከሩቅ ሀገር ተሰማ። በተቀረፁ ምስሎቻቸውና በባዕድ ከንቱነትስ ያስቈጡኝ ስለ ምንድን ነው? 20መከሩ አልፎአል፤ በጋውም ዐልቋል፤ እኛም አልዳንንም። 21በሕዝቤ ሴት ልጅ ስብራት እኔ ወድቄ ተሰብሬአለሁ፤ ጠቍሬማለሁ፤ ራስ ማዞርም ይዞኛል፤ ምጥ እንደያዛትም ሴት በመከራው እጨነቃለሁ።#“ምጥ እንደያዛትም በመከራው እጨነቃለሁ” የሚለው በዕብ. የለም። 22በገለዓድ መድኀኒት የለምን? ወይስ በዚያ ሐኪም የለምን? የወገኔ ሴት ልጅ ፈውስ ስለ ምን አልሆነም?
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 8: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ